በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ በኃይል አቅርቦት የኢንቨስትመንት ዕድሎች የሚሰማራበት ምቹ ምኅዳር ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ በኃይል አቅርቦት የኢንቨስትመንት ዕድሎች የሚሰማራበት ምቹ ምኅዳር ተፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ በኃይል አቅርቦት የኢንቨስትመንት ዕድሎች የሚሰማራበት ምቹ ምኅዳር መፈጠሩን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) ገለጹ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት በፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ የሶላር ሚኒግሪድና የሶላር ፓርክ ፕሮጀክት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።
የሁለትዮሽ የትብብር ስምምነቱ በፀሐይ ኃይል ፓርክና የሶላር ሚኒ ግሪድ የኃይል ማመንጫ፣ በመስኖና መጠጥ ውሃ አቅርቦት የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ትብብር ዕድሎችን የሚያመቻች መሆኑ ተገልጿል።
በዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት አዘጋጅነት በፀሐይ ኃይል ልማት የፋይናንስ ዕድሎች ዙሪያ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የሙያተኞች የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በዚሁ ጊዜ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር)÷ የፀሐይ ኃይል ልማት ተደራሽነት የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።
ለዚህም በመንግስት የግል አጋርነት የኃይል ልማት በተሻለ ሁኔታ ማስፋት የሚያስችል ምቹ ምኅዳር መፍጠር እንደተቻለ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለግሉ ዘርፍ ክፍት አድርጋለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው÷ በታዳሽ የኃይል ልማትም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል ሥርዓት መፈጠሩን አንስተዋል።
የግሉ ዘርፍ የልማት ተዋናዮችም በኢትዮጵያ የፀሐይ ኃይልና የግብርና ልማት የኢንቨስትመንትን ማሳደግ የሚያስችል ፖሊሲ ስራ ላይ መዋሉን አስገንዝበዋል።
መንግስት ከዓለም አቀፉ የፀሐይ ኃይል ጥምረትና የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሰራ አንደሚገኝ አንስተዋል።
የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት ዋና ዳይሬክተር አሺሽ ከሀና÷ በፀሐይ ኃይል ልማት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የፋይናንስ አቅርቦትን ማጎልበት ያስፈልጋል ብለዋል።
የፀሐይ ኃይል ልማትን ለማሳደግም ቤተ-ሙከራ፣ የወጣቶች የፈጠራ ክህሎት ማዕከላትና የፋይናንስ አቅርቦት ወሳኝ ሚና አንዳላቸው ተናግረዋል።
በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ አነስተኛ የኤሌክትሪክ አቅርቦቶችን በማስፋት የውሃ ፓንፖችን ለማልማት ድጋፍ እንደሚደርጉ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የፀሐይ ኃይል ልማት ማኅበር ዋና ዳይሬክተር የምስራች ሲሳይ÷ በዘርፉ ላይ በፖሊሲ ማማከር፣ የፋይናንስ ማፈላለግና የአቅም ግንባታ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአርሶ አደሩን ማህበረሰብ የግብርና ልማት ምርታማነት ለማሳደግም የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትና የግብርና ግብዓት የሶላር ቴክኖሎጂዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ሊቀርቡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የዓለም አቀፍ የፀሀይ ኃይል ጥምረት ኢትዮጵያን ጨምሮ 124 አባል ሀገራትን በማቀፍ የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ ልማትን ለማስፋፋት እየሰራ የሚገኝ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው።