የኦሮሚያ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ለአንድ ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ለአንድ ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

አምቦ፤ ነሐሴ 8/2017(ኢዜአ)፡- የኦሮሚያ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ በአምቦ ከተማ ድጋፍ ለሚሹ ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ዛሬ አበርክቷል፡፡
የኦሮሚያ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሁሴን ኡሹ እንደገለጹት ድጋፉ የተደረገው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ቤተሰብ ተማሪዎችን ለማገዝ ነው።
የተደረገው ድጋፍ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ደብተር እና እስክሪብቶ መሆኑንም ገልፀዋል።
የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አጫሉ ገመቹ ለተማሪዎች ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ በቀጣይም ሌሎች ድርጅቶች መሰል ድጋፎችን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በከተማው ድጋፍ ከተደረገላቸው ቤተሰቦች መካከል ዳንደና ነገሪ በሰጡት አስተያየት፤ ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት እንደሚቸገሩ አስታውሰዋል።
ዛሬ የተደረገላቸው የደብተርና እስክርብቶ ድጋፍ ችግራቸውን እንዳቃለለላቸው ጠቁመው አመስግነዋል፡፡
የአራተኛ ክፍል ተማሪ ረቢራ ወርቅነህ በተደረገለት ድጋፍ ደስተኛ መሆኑን ገልጾ ትምርቱንም በርትቶ መማር እንደሚያስችለው ተናግሯል።
የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ዋንኦፊ ሙለታ የተደረገላት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በርትታ በማጥናት ለተሻለ ውጤት ለመብቃት እንደሚያግዛት ገልጻለች።