ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ለሚካሄደው ሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል

ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 8/2017(ኢዜአ)፦ በድሬደዋ ከነገ ጀምሮ ለሚካሄደው ሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የድሬዳዋ አስተዳደር እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የ2017 የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ገለጸ።

ከነገ ነሐሴ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫ ይካሄዳል።

በድሬዳዋ አስተዳደርም ምርጫውን ማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የድሬዳዋ አስተዳደር እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የ2017 የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ሰብሳቢ ሼህ አብዱልጀሊል ዑስማን አህመድ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ቦርዱ በየደረጃው በሚገኙ መስጂዶች ለምርጫው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ከማሟላት ጀምሮ ሁሉንም ዝግጅቶች አጠናቋል ነው ያሉት።

መራጮች በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘትና በመምረጥ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የዘንድሮው ምርጫ በ49 ሺህ 92 መስጅዶች፣ 13 ሚሊዮን 151 ሺህ 889 ህዝበ ሙስሊም ተመዝግቦ ምርጫውን እየተጠባበቀ መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የምርጫ ምዝገባ ሂደቱ ወሳኝ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት እንደነበር በመግለፅ፤ የምርጫ ሂደቱን ለማስፈጸም ከመስጅድ እስከ ፌደራል ድረስ ከ455 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል።

የመጅሊስ ምርጫው ነገ በኡለማዎች ዘርፍ ምርጫ የሚጀመር ሲሆን፥ ሂደቱን ጠብቆ እስከ ፌደራል ድረስ እንደሚከናወንና ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም