ቀጥታ፡

ማህበሩ ጥራቱ የተጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እንዲቀርብ እየሰራ ይገኛል

አዳማ፤ ነሐሴ 8/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት በማጠናከር ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እንዲቀርብ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

ማህበሩ የቡና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና ጥራቱን ማስጠበቅ በሚቻልበት ሂደት ላይ ከአርሲና ምዕራብ አርሲ ዞኖች የተውጣጡ የቡና አምራች አርሶ አደሮችና አቅራቢዎች ጋር በአዳማ ውይይት አካሂዷል።


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር ፕሬዚዳንት ሁሴን አምቦ(ዶ/ር) በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት የቡና ጥራት ለማስጠበቅና ምርቱን ለማሳደግ እየተደረገ ባለው ጥረት አምራቾችና አቅራቢዎችን በቀጥታ ለማሳተፍ የንቅናቄ ስራ እየተሰራ ነው።

የዛሬው ውይይትም በአምራቾች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎች መካከል ያለው የጥራት እሴት ሰንሰለት ትብብር እንዲጠናከር፣ የጥራት ቁጥጥርና የምርት አቅርቦት በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ማህበሩ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ከአምራች እስከ ቡና ላኪዎች ድረስ የተቀናጀ የቡና ጥራት ማስጠበቅና ምርት መጨመር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በእስካሁኑ ጥረትም ልዩ ጣዕም ያለው(ስፔሻሊቲ) ቡና በጥራት በማዘጋጀትና ወደ ዓለም ገበያ በመላክ ምርቱ ሰፊ ተቀባይነት እንዲያገኝ መደረጉንም አስታውሰዋል።

የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አጥናፉ ደምሴ፤ በተያዘው በጀት ዓመት በአምራቾች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎች ዘንድ የሚታየውን የጥራት ጉድለት ለመቅረፍ እስከ አርሶ አደሮች ድረስ ንቅናቄ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በተለይ በቡና ምርት አሰባሰብ፣ በማጓጓዝና በሚላክበት ወቅት የሚኖረውን የጥራት ጉድለትና ብክነትን ለማስወገድ 

ከክልሉ ግብርና ቢሮ፣ ከቡናና ሻይ ባለስልጣንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል።

በክልሉ የቡና የጥራት እሴት ሰንሰለትን ለማስጠበቅ ተጨማሪ የቡና ቅምሻና ሰርቲፊኬሽን ማዕከላት በምዕራብ ጉጂና በምዕራብ ወለጋ እንደሚከፈቱም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የቡና ምርት የእርጥበት መለኪያ ማሽኖች ለ19 አምራች ወረዳዎች መሰራጨቱን ጠቅሰው በቀጣይ ለሁሉም ዞኖች ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል።


 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አርሶ አደር ዳንኤል ውቅታዬ፤ በባለሙያዎች የተደገፈ ትምህርትና ግንዛቤ በማግኘታቸው ቡናን በተሻለ ጥራት እያመረቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በመትከል ምርትና ምርታማነትን እያሳደጉ መሆኑን ጠቅሰው ቀይ ቡና ብቻ በመሰብሰብ ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን አመልክተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም