ቀጥታ፡

ሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫ ነገ በኡለማዎች ዘርፍ ምርጫ ይጀመራል -የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2017(ኢዜአ)፦ የ2017 ሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫ ነገ በኡለማዎች ዘርፍ ምርጫ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ገለጸ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ሀገራዊ የመጅሊስ ምርጫ ምዝገባ መጠናቀቁን እና የምርጫ ቀን ሁነቶችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

የምርጫ አስፈፃሚ ቦርዱ ሰብሳቢ አብዱላዚዝ ኢብራሂም (ዶ/ር)፤ የ2017 የመጅሊስ ምርጫ ለህዝበ ሙስሊሙ ታሪካዊ ነው ብለዋል።

በመጅሊስ ምርጫው ኡለማዎች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች ሴቶችና የስራ ማህበራት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

የምርጫ ቁሳቁሶች ወደ የምርጫ ጣቢያው መጓጓዛቸውን ገልጸዋል።

ለ2017 ዓ.ም የመጅሊስ ምርጫ አጠቃላይ የመራጮች ምዝገባ መደረጉን አውስተዋል።

በመጅሊስ ምርጫው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የኡለማዎች ምርጫ በነገው ዕለት ከጁምአ እና ሶላት በኋላ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

የዘንድሮው ምርጫ በ49 ሺህ 92 መስጅዶች፣ 13 ሚሊዮን 151 ሺህ 889 ህዝበ ሙስሊም ተመዝግቦ ምርጫውን እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጸዋል።

የምርጫ ምዝገባ ሂደቱ ወሳኝ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት እንደነበር በመግለፅ፤ የምርጫ ሂደቱን ለማስፈጸም ከመስጅድ እስከ ፌደራል ድረስ ከ455 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

የመጅሊስ ምርጫው ሂደቱን ጠብቆ እስከ ፌደራል የሚካሄድ መሆኑን ገልጸው፤ ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ይጠናቀቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም