ቀጥታ፡

ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎትን ለማስፋት የህክምና መሳሪያዎችን ማሟላት ላይ ትኩረት ተደርጓል - ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2017(ኢዜአ)፦ ለዜጎች ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎትን ለማስፋት የህክምና መሳሪያዎችን ማሟላት ትኩረት እንደተሰጠው የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ።

ጤና ሚኒስቴር ከ4 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የህክምና መሳሪያዎችን ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አስረክቧል።


 

በዚህ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደገለፁት መንግስት የተሻሻለ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እያከናወነ ባለው ተግባር አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።

የህክምና ተቋማትን ማስፋፋት የህክምና መሳሪያዎችና የመድሃኒት አቅርቦትን ማሟላትና የዘርፉን ሙያተኞች አቅም መገንባት ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ዛሬ በኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት በኩል ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተደራሽ የተደረገው የህክምና መሳሪያ የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

የህክምና መሳሪያዎቹ ዲጂታል የኤክስሬይ መመርመሪያ ማሽኖች፣ የቀዶ ህክምና መሳሪያዎች፣ የተለያዩ የጤና መመርመሪያ ግብዓቶችና የንጽህና መስጫ ላውንደሪ ማሽኖች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ይህም የጤና አገልግሎትን ለማዘመንና ተደራሽ ለማድረግ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ነው የገለፁት።

የህክምና መሳሪያዎቹ አጠቃላይ ወጪ ከ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑንና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለክልሎች የማሰራጨት ስራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

በዚህ ሒደት የህክምና መሳሪያዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ለደረሰባቸውና እጥረት ላለባቸው የጤና ተቋማት ቅድሚያ እንደሚሰጥም ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፥ የህክምና መሳሪያዎቹ በየክልሉ ለሚነሱ የግብዓት አቅርቦት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።

ፍትሐዊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ አይነተኛ ሚና እንዳላቸው በመጠቆም፥ የሚፈለገውን የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡና ማህበረሰቡን እንዲጠቅሙ በጥንቃቄና በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል ነው ያሉት።


 

የህክምና መሳሪያዎቹን ከተረከቡ ክልሎች መካከል የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ፕሮፌሰር ነጻነት ወርቅነህ፥ የህክምና መሳሪያዎቹ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፉ መሆናቸው ቀልጣፋና ጥራቱን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።


 

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱልከሪም መንግስቱ በበኩላቸው የህክምና መሳሪያዎቹ ህብረተሰቡ በአቅራቢያው ህክምና እንዲያገኝ ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው ጠቁመዋል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ኢብራሒም ተማም፥ የህክምና ቁሳቁሶቹ በክልሉ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማሻሻል አጋዥ ናቸው ብለዋል።


 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም