ቀጥታ፡

በተያዘው የመኸር ወቅት ሀምሳ ሺህ ሜትሪክ ቶን ምርት ወደ መጠባበቂያ ክምችት ይገባል

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 8/2017(ኢዜአ)፦በተያዘው የ2017/18 ዓ.ም የመኸር ወቅት ሀምሳ ሺህ ሜትሪክ ቶን ምርት ወደ መጠባበቂያ ክምችት ለማስገባት ግብ መቀመጡን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)÷ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከተቀመጡ ግቦች መካከል የመጠባበቂያ ክምችት አቅምን ማሳደግ ዋነኛው ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሁሉም የግብርና ምርታማነት መስኮች የምታስመዘግበው አመርታም የሀገርን የአደጋ ጊዜ የመጠባበቂያ ክምችት አቅም በማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልል መንግስታትም የመጠባበቂያ ክምችት አቅም በማሳደግ የዕለት ደራሽ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚያቀርቡበት አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የመጠባባቂያ እህል ክምችት የሰብል ምርታማነትን አቅምን ማሳደግ የሚያስችል የ3 ቢሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ እንደተላለፈላቸው አስታውቀዋል።

አሁን ላይ ቅጽበታዊ አደጋዎችን ምላሽ መስጠት የሚያስችል የ500 ሺህ ሜትሪክ ቶን የመጠባበቂያ እህል ክምችት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በተያዘው የ2017/18 መኸር ወቅት በመጀመሪያ ዙር 50 ሺህ ሜትሪክ ቶን የሰብል ምርት ወደመጠባበቂያ ክምችት ለማስገባት ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ክልሎችም ባላቸው የግብርና ምርታማነት አቅም መሰረት የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ ለመጠባበቂያ የሰብል ክምችት የሚውል ምርት ለኮሚሽኑ እንደሚያስተላልፉ አንስተዋል።

ኮሚሽኑ ለመጠባበቂያ ክምችት የሚውለውን እህል በዚህ መልኩ ማድረጉ ለገበያ መረጋጋት ጉልህ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።

እንዲሁም ምርትን በብዛት ለማምረት እድል የሚፈጥር በመሆኑ ለምርትና ምርታማነት መጨመር ጉልህ ሚና እንዳለው ነው የገለጹት።

ለዚህ ስራ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚመራ አስተባባሪ ኮሚቴ የተዋቀረለት ሲሆን የፋይናንስ እጥረት የሚያጋጥማቸውን ክልሎች ለመደገፍ ያግዛል ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል  አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ጋንታ ጋምአ በበኩላቸው፤ በክልሉ የጸደቀው የአደጋ ስጋት መጠባበቂያ ፈንድ ደንብ ለአደጋ ጊዜ ሀብት የመሰብሰብና እና ምላሽ የመስጠት አቅም ለማሳደግ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።  


 

ለአብነትም ባለፈው ዓመት ለአደጋ ጊዜ ምላሽ ከ22 ሺህ 600 ኩንታል በላይ መጠባበቂያ እህል ክምችት መያዙን ገልጸዋል።

ዘንድሮም ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል በተሰራው ሥራ 1 ቢሊዮን ብር የመጠባበቂያ ፈንድ ለማስቀመጥ ከመቻሉ ባለፈ 6 ሺህ 300 ሄክታር መሬት በማረስ የምግብ እህል ክምችትን ለማሳደግ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም