በቻን ውድድር የምድብ አንድ ጨዋታዎች ተጠባቂ ናቸው 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2017(ኢዜአ)፦ 12ኛ ቀኑን ባስቆጠረው የስምንተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና (ቻን) የምድብ አንድ ሶስተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።

ሞሮኮ ከዛምቢያ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በካሳራኒ ስታዲየም ይጫወታሉ።


 

በሁለት የምድብ ጨዋታዎቿ ሶስት ነጥብ ያገኘችው ሞሮኮ በሶስት ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በአንጻሩ ዛምቢያ እስከ አሁን ባደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች ተሸንፋ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አምስተኛ ደረጃን ይዛለች።

ሞሮኮ ካሸነፈች ወደ ሩብ ፍጻሜ የመግባት እድሏን የበለጠ ታሰፋለች። ተጋጣሚዋ ዛምቢያ በውድድሩ ላይ ለመቆየት ከዛሬው ጨዋታ ሶስት ነጥብ መውሰድ አለባት።

ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 20 ጨዋታዎች ሞሮኮ 12 ጊዜ ስታሸንፍ ዛምቢያ 6 ጊዜ ድል ቀንቷታል። 2 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

በዚሁ ምድብ ምሽት 2 ሰዓት ላይ አንጎላ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

አንጎላ በአራት ነጥብ ሁለተኛ፣ የሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ማሸነፍ ለሁለቱም ቡድኖች ወደ ሩብ ፍጻሜው የማለፍ እድላቸውን ከፍ ያደርገዋል።

ሀገራቱ 13 ጨዋታዎችን እርስ በእርስ አድርገው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 7 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች። አንጎላ 2 ጊዜ ስታሸንፍ 4 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

ቻን በኬንያ፣ ታንዛንያ እና ዩጋንዳ ጣምራ አዘጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል። ውድድሩ በአገር ውስጥ ሊግ የሚገኙ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም