በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ566 መስጅዶች የመጅሊስ ምርጫ ለማካሄድ የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ566 መስጅዶች የመጅሊስ ምርጫ ለማካሄድ የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል

አሶሳ፤ ነሐሴ 08/2017 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ566 መስጅዶች የመጅሊስ ምርጫ ለማካሄድ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሐጂ ጀማል ኡመር ለኢዜአ እንደተናገሩት ቦርዱ በክልሉ በስምንት ክላስተር ለምርጫው አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል።
በተለያዩ ዘርፎች የሚደረገው የመጅሊስ ምርጫ በክልሉ በ566 መስጅዶች የሚካሄድ መሆኑን ገልጸው ለድምጽ አሰጣጡም የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
የምርጫውን ሂደት ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ በሆነ መልኩ ለማስኬድ በቦርዱ በኩል ዝግጅት መጠናቀቁንም አረጋግጠዋል።
በተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን የተናገሩት የቦርዱ ሰብሳቢ መራጮች በእለቱና በሰአቱ በመገኘት ድምፃቸውን እንዲሰጡም አስገንዝበዋል።
በክልሉ የድምጽ አሰጣጡ በነገው ዕለት ከጁመአ ሶላት በኋላ በየመስጅዶች በዑለሞች ምርጫ የሚጀመር መሆኑን የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።