የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል-ፕላንና ልማት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል-ፕላንና ልማት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 8/2017(ኢዜአ)፦የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ገለጹ።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም እንደምታስተናግድ ይታወቃል።
ጉባኤው "ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፥ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል መሪ ሀሳብ ይካሄዳል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ጉባኤውን በተመለከተ ከግሉ ዘርፍ እና የፋይናንስ ተቋማት አመራሮች ጋር በአዲስ አበባ እየተወያየ ነው።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳሉት ለሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
ጉባኤው ለሰው ልጆች ፈተና የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል እና ለመቋቋም የሚያስችሉ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ትልቅ ጉባኤ መሆኑን ገልጸዋል።
ጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቅረፍ በርካታ የመፍትሄ ሀሳቦች የሚቀርቡበት እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ የሚሆኑ አህጉራዊ አቅሞች የሚፈጠሩበት መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ በጉባኤው በአጀንዳነት ከተያዙ ጉዳዮች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ በግሉ ዘርፍ ላይ እያሳደረ ያለው ተጽእኖ አንዱ ነው።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ ተጨባጭ ስራ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
በጉባኤው የኢትዮጵያ ምርጥ ተሞክሮዎች እንደሚቀርቡ ጠቁመው፥ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት አመላክተዋል።
የግሉ ዘርፍ ተዋንያን በሙያ፣ በገንዘብ እንዲሁም በሀሳብ በማገዝ በጉባኤው አዎንታዊ ሚና መጫወት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አፍሪካውያን ድምጻቸውን ከማሰማት ባሻገር ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ በግንባር ቀደምነት እየሰሩ መሆኑን ለዓለም የሚያሳዩበት መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል።