የህዳሴ ግድብ የሚገኝበት አካባቢ የሚተከሉ ችግኞች የግድቡን ህልውና የሚጠብቁ ናቸው

አሶሳ፤ ነሐሴ 08/2017 (ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገኝበት አካባቢ የሚተከሉ ችግኞች የግድቡን ህልውና የሚጠብቁ ናቸው ሲሉ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስ ተናገሩ። 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ምርታማነትን በማሳደግ እንደ ሀገር ከተረጂነት  ለመውጣት ለሚደረገው  ጥረት ከፍተኛ እገዛ  እንዳለውም ተገልጿል። 

የፌዴራል ተቋማት አመራሮችና የየክልሉ ነዋሪዎች በክረምቱ ወራት ሰፋፊ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚገኝበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም የተለያዩ ወረዳዎች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፌዴራል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ግድቡ የሚገኝበት አካባቢ የሚተከሉ ችግኞች በተለይም የግድቡን ህልውና ዘላቂ የሚያደርጉ መሆናቸውን አንስተዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው  ችግኞች በመትከሉ ረገድ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከዕቅድ በላይ መከናወኑን ገልጸዋል።

በተለይም አገሪቷ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለምታደርገው ግስጋሴ ፈተና የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የአረንጓዴ አሻራን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ ለሚመጡ ጫናዎች ተጨባጭ ምላሽ የሚሰጥ እርምጃ መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተተከሉ መሆኑን አንስተው፤ በተለይም የህዳሴ ግድብ የሚገኝበት አካበቢ የሚተከሉ ችግኞች ግድቡ በደለል እንዳይሞላ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን ከ200 ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል ሀገራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም አንስተዋል።

በመጪው ጳጉሜ ወር ላይ የሚካሄደው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ አሻራ የሰጠችውን ትኩረት በተጨባጭ የምታሳይበት እንደሆነም አብራርተዋል።

ጉባኤው በኢትዮጵያ እንዲካሄድ መወሰኑ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት አገሪቷ እያከናወነችው ያለውን ተሞክሮ በተለያዩ ሀገራት ለማስፋፋት ዕድል የሚፈጥር እንደሆነም ገልጸዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር በክልሉ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራትና የችግኝ ተከላ መርሃግብር ማከናወናቸው ይታወሳል ።

በመርሃግብሩ ላይ የሚኒስቴሩ እና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም