የመጅሊስ ምርጫ ህዝበ ሙስሊሙ በፍላጎቱ የሚሻለውን መሪ የሚመርጥበት እና ጠንካራ ተቋም የሚገነባበት እድል የሚያገኝበት ነው - ኡስታዝ በድሩ ኑሩ - ኢዜአ አማርኛ
የመጅሊስ ምርጫ ህዝበ ሙስሊሙ በፍላጎቱ የሚሻለውን መሪ የሚመርጥበት እና ጠንካራ ተቋም የሚገነባበት እድል የሚያገኝበት ነው - ኡስታዝ በድሩ ኑሩ

ክልል፤ነሐሴ 8/2017(ኢዜአ)፦ የመጅሊስ ምርጫ ህዝበ ሙስሊሙ በፍላጎቱ የሚሻለውን መሪ የሚመርጥበት እና ጠንካራ ተቋም የሚገነባበት እድል የሚያገኝበት መሆኑን የኦሮሚያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ኡስታዝ በድሩ ኑሩ ገለጹ።
የምክር ቤቱ የመጅሊስ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ኡስታዝ በድሩ ኑሩ በምርጫው ዙሪያ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ለምርጫው ዝግጅት ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል።
በእነዚህ ጊዜያትም የመስጊድ፣ የወረዳ፣ የዞንና የክልል አስመራጭ ኮሚቴዎችን የማዋቀር ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ጎን ለጎን ለሙስሊሙ ማህበረሰብ አጠቃላይ ምርጫውን አስመልክቶ ግንዛቤ የማሳደግ ስራ በስፋት መከናወኑን ገልጸዋል።
በመቀጠልም የመራጮች ምዝገባ እና የምርጫ ቁሳቁስ የማድረስ ተግባራት በማከናወን ህዝቡ ለምርጫ ዝግጁ ሆኗል ብለዋል።
የምርጫ ሂደቱም በአምስት ዘርፎች ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን የኡለማዎች ዘርፍ፣ የምሁራን፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የሰፊው ማህበረሰብ ዘርፍ ተብሎ ተከፍሎ ይካሄዳል ብለዋል።
ሁሉም እንደየዘርፉ ከመራጮች ጋር የትውውቅ መድረክ ሲያካሄድ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ምርጫው በዓይነቱ የመጀመሪያ በመሆኑም ስራው ሰፊ ጊዜ ወስዷል ነው ያሉት።
ከዚህ በፊት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ይጠቅመኛል፣ ይወክለኛል የሚለውን መሪ በትክክል ለመምረጥ እድል እንዳልነበረው አንስተው፤ ምርጫው በዚህ መልኩ መደረጉ ህዝቡ በፍላጎቱ የሚሻለውን መሪ የሚመርጥበት እድል ያመቻቸ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈ ህዝበ ሙስሊሙ የሚመራበትን ጠንካራ ተቋም የሚገነባበት ምቹ አጋጣሚ እንደሆነም አክለዋል።
በተለይም በየአካባቢው የሚገኙ ኃይማኖታዊ እውቀታቸው የላቀ ግለሰቦችን ወደ መጅሊስ ለማምጣት ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ጊዜም አጠቃላይ የምርጫው ዝግጅት በመጠናቀቁ ህዝበ ሙስሊሙ በነቂስ ወጥቶ በምርጫው እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
ለምርጫው መሳካትም ሁሉም ባለድርሻ አካላት አስፈላጊ ድጋፍ ማድረጋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።