ቀጥታ፡

ህዝበ ሙስሊሙ በመጅሊስ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ ጠንካራ ኢስላማዊ ተቋም በመገንባት ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል

ሐረር ፤ነሐሴ 8/2017(ኢዜአ)፦  ህዝበ ሙስሊሙ በመጅሊስ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ ጠንካራ ኢስላማዊ ተቋም በመገንባት ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የሐረሪ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የምርጫ ቦርድ ገለጸ።

በአምስት የተለያዩ ዘርፎች የሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ ከነሐሴ 9 እስከ 11 ቀን 2017 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከወረዳ እስከ ፌደራል በየመስጅዶች የሚካሄድ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህም መሰረት በሐረሪ ክልል ለሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ የተደረገውን ዝግጅት በተመለከተ ኢዜአ የክልሉን እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚ ሰብሳቢ ሸህ አብዱረሃማን መሐመድን አነጋግሯል።

ሸህ አብዱረሃማን በማብራሪያቸውም በክልሉ አካታችና አሳታፊ የመጅሊስ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው በድምፅ መስጫው እለት ህዝበ ሙስሊሙ በነቂስ በመሳተፍ መሪዎቹን እንዲመርጥ ጠይቀዋል።

የምርጫው ሂደት የተሟላ፣ ነፃና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን አንስተው ይህንን መልካም አጋጣሚ ህዝበ ሙስሊሙ በአግባቡ እንዲጠቀምበት አስገንዝበዋል።

የምርጫው ዓላማ ጠንካራ እስላማዊ ተቋም እና ብቁ አመራሮችን የመፍጠር በመሆኑ በዚህ ሂደት ህዝበ ሙስሊሙ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከወረዳ እስከ ፌደራል የመጅሊስ ምርጫ ከነሐሴ 9 እስከ ነሐሴ 11 ቀን 2017 ዓ.ም በመስጅዶች የሚካሄድ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም