በጋምቤላ ክልል በሀገር አቀፍ ደረጃ ከነገ ጀምሮ ለሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል በሀገር አቀፍ ደረጃ ከነገ ጀምሮ ለሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል

ጋምቤላ፤ነሐሴ 8/2017(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል በሀገር አቀፍ ደረጃ ከነገ ጀምሮ ለሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ አስታወቀ።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሐጂ አማረ አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ከነገ ነሐሴ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ከወረዳ እስከ ሀገር አቀፍ ለሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ በጋምቤላ የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል።
ቦርዱ ከክልል እስከ ወረዳ በሚገኙ መስጊዶች ለምርጫው የሚያስፈልጉ ግብዓት ማሟላትን ጨምሮ የቅደመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀው ዕለቱ እየተጠበቀ ነው ብለዋል።
የመራጮች ምዝገባ ተጠናቆም ተመራጮች በየመስጊዱ እራሳቸውን በማስተዋወቅ ለምርጫው መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ከነገ ነሐሴ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ መራጮች የሚወክሏቸውን የመምረጥ ሂደት የሚጀምሩበት ጊዜ እንደሚሆንም ገልጸዋል።
የዘንድሮው ምርጫ ህዝበ ሙስሊሙ ይወክሉኛል የሚላቸውን የመጅሊስ አመራር ለመጀመሪያ ጊዜ በካርድ የሚመርጥበት እድል ያገኘበት በመሆኑ ምርጫውን ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
በመሆኑም በዚህ ልዩ አጋጣሚ ህዝበ ሙስሊሙ በንቃት በመሳተፍ የሚወክሉትን አመራሮች በመምረጥ ጠንካራ ተቋምና ብቁ አመራሮችን የማፍራት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል ።