ፒኤስጂ ቶተንሃም ሆትስፐርስን በማሸነፍ የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን አነሳ - ኢዜአ አማርኛ
ፒኤስጂ ቶተንሃም ሆትስፐርስን በማሸነፍ የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን አነሳ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2017(ኢዜአ)፦ በአውሮፓ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ፒኤስጂ ቶተንሃም ሆትስፐርስን በመለያ ምት በመርታት አሸናፊ ሆኗል።
ማምሻውን በጣልያን በሚገኘው ብሉኢነርጂ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሚኪ ቫን ደ ቬን በ39ኛው እና ክርስቲያን ሮሜሮ በ48ኛው ደቂቃ ባሳረፉት ጎል ቶተንሃም ሆትስፐር መሪ ሆኖ ነበር።
ቶተንሃም አሸነፈ ሲባል ተቀይረው የገቡት ካንግ ኢን ሊ በ85ኛው ደቂቃ እና ጎንካሎ ራሞስ በ93ኛው ደቂቃ ባስቆጠሩት ግብ ፒኤስጂ አቻ ሆኗል።
ቡድኖቹ በመደበኛው 90 ደቂቃ ሁለት አቻ በመለያየታቸው ጨዋታው ቀጥታ ወደ መለያ አምርቷል።
በዚህም ፒኤስጂ 4 ለ 3 በማሸነፍ የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ አንስቷል።
ፒኤስጂ ፍሰት ያለው ኳስ ለመጫወት የተቸገረ ሲሆን በተከላካይ፣ የአማካይ እና አጥቂ ክፍሎቹ ላይ የቅንጅት ችግር ታይቷል።
ቡድኑ በመጨረሻዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች ያሳየው ማንሰራራት ወደ ጨዋታው እንዲመለስ አድርጎታል።
ሉዊስ ኤነሪኬ ጣልያናዊውን ግብ ጠባቂ ጂያንሉዊጂ ዶናሩማን ከዛሬ ጨዋታ ስብስብ ውጪ ማድረጋቸው ትችት እንዲያስተናግዱ አድርጓቸዋል።
ፒኤስጂ በውድድር ዓመቱ አምስተኛ ዋንጫውን በማንሳት ድንቅ የውድድር ዓመቱን በደማቅ ሁኔታ አሳርጓል።
ቶተንሃም ሆትስፐርስ በጨዋታው በተደራጀ መከላከል፣ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ እና በቆሙ ኳሶች በመጠቀም የተሻለ ብቃት አሳይቷል።
የሰሜን ለንደኑ ቡድን ከዩሮፓ ሊግ ቀጥሎ ሁለተኛ ዋንጫውን የማንሳት ህልሙ አልተሳከም።
የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እና የዩሮፓ ሊግ አሸናፊ የሚያደርጉት ጨዋታ ነው።