የመጅሊስ ምርጫ ለህዝበ ሙስሊሙ ጠንካራ ተቋም የመገንባት እና ብቁ አመራሮችን የመፍጠር ሂደት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመጅሊስ ምርጫ ለህዝበ ሙስሊሙ ጠንካራ ተቋም የመገንባት እና ብቁ አመራሮችን የመፍጠር ሂደት ነው

ባሕር ዳር ፤ ነሐሴ 7/2017(ኢዜአ)፦የመጅሊስ ምርጫ ለህዝበ ሙስሊሙ ጠንካራ ተቋም የመገንባት እና ብቁ አመራሮችን የመፍጠር ሂደት በመሆኑ በምርጫው ሁሉም የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የምርጫ ቦርድ ገለጸ።
የከፍተኛ ምክር ቤቱ የቦርድ ሰብሳቢ ሙሐመድ ይማም (ዶ/ር)፤ ቦርዱ 3 ሺህ 12 የምርጫ ጣቢያዎችን በማቋቋምና ከ27 ሺህ በላይ ምርጫ አስፈፃሚዎችና ታዛቢዎች ተሰማርተው የመራጮች ምዝገባ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2017 ዓ.ም መካሄዱን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት ከነሀሴ 9 አስከ 11 ቀን 2017 ዓ.ም በየመስጅዶች ለሚካሄደው ምርጫ የተሟላ ዝግጅት በማድረግ እለቱ እየተጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ዑላማዎች፣ ምሁራን፣ ሴቶችና ወጣቶችን ጨምሮ በተቀመጡት የምርጫ ዘርፎች ለሚካሄደው ምርጫ ህዝበ ሙስሊሙ በንቃት በመሳተፍ በየደረጃው ያሉ መሪዎችን እንዲመርጥ ጥሪ አቅርበዋል።
የመጅሊስ ምርጫ ለህዝበ ሙስሊሙ ጠንካራ ተቋም ከመገንባትም ባለፈ ለህብረ ብሔራዊ ሀገረ መንግስት ግንባታ የላቀ ትርጉም ያለው በመሆኑ በእለቱ ይህንን መልካም አጋጣሚ እንዲጠቀም ጥሪ አቅርበዋል።
በምርጫውም የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አባላትና ሥራ አስፈፃሚዎች እንዲሁም ለፌዴራል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሚወከሉ ዕጩዎች ይለያሉ ብለዋል።
የመጅሊስ ምርጫ ለህዝበ ሙስሊሙ ጠንካራ ተቋም የመገንባት ጥረት ከማገዝም ባለፈ ለህብረ ብሔራዊ ሀገረ መንግስት ግንባታ ያለውን ጠቀሜታ በቅጡ በመረዳት ህዝበ ሙስሊሙ በዕለቱ በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት መሪዎቹን ይመርጥ ዘንድ አስገንዝበዋል።
ከነሀሴ 9 እስከ 11 ቀን 2017 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከወረዳ እስከ ፌደራል የመጅሊስ ምርጫ በመስጂዶች እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።