ማዳጋስካር ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝታለች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2017(ኢዜአ)፦ በስምንተኛው የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒዮና (ቻን) የምድብ ሁለት መርሃ ግብር ማዳጋስካር ማዕከላዊ ሪፐብሊክን 2 ለ 0 አሸንፋለች።

በቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቶኪ ኒያና ራኮቶንድራቤ እና ላላና ራፋኖሜዛንትሶአ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

በጨዋታው ማዳጋስካር በተጋጣሚዋ ላይ ብልጫ ወስዳለች።

ውጤቱን ተከትሎ ማዳጋስካር በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ሩብ ፍጻሜ የመግባት እድሏን አለምልማለች።

ሶስተኛ ሽንፈቷን ያስተናገደችው ማዕከላዊ ሪፐብሊክ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ከውድድሩ ተሰናብታለች።

በዚሁ ምድብ በአሁኑ ሰዓት ሞሪታንያ ከቡርኪናፋሶ ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ።

ምድቡን በዘጠኝ ነጥብ የምትመራው ታንዛንያ ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፏ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም