ስትራቴጂክ አመራር የማፍራት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል -የመከላከያ ዋር ኮሌጅ - ኢዜአ አማርኛ
ስትራቴጂክ አመራር የማፍራት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል -የመከላከያ ዋር ኮሌጅ
ሠመራ፣ነሐሴ 7፣2017 (ኢዜአ) ስትራቴጂክ አመራር ለማፍራት በሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አስታወቀ።
ኮሌጁ በአፋር ክልል ለሚገኙ የፀጥታ አመራሮች በቀጣይ በአቅም ግንባታ ስልጠና አብሮ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ዙሪያ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ አካሂዷል።
የኮሌጁ ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ኪሮስ ሃጎስ በወቅቱ እንደገለጹት ኮሌጁ ላለፉት ዓመታት ስትራተጂክ መሪዎችን ለማፍራት የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ሲሰጥ ቆይቷል ።
በአገር ደህንነት፣ በአመራር ስትራቴጂና የኢትዮጵያ ጥቅም በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ ስልጠናዎችን በመስጠት የራሱን አበርክቶ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከፌዴራልና ከክልል ፀጥታ አካላት ጋር በጋራ መስራት የሚቻልበትን ሁኔታ ሲፈጥር መቆየቱንም አንስተዋል።
በቀጣይም መሰል የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
የአፋር ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ሁመድ በበኩላቸው መድረኩ ከኮሌጅ ጋር ለመስራት የሚያስችል የፍላጎት ልየታ ለማድረግ አቅም መፈጠሩን ተናግረዋል ።
”መድረኩ በአገራዊ ጉዳይ ላይ ተጨባጭ ዕውቀት መጨበጥ ያስቻለ ነው” ያሉት ደግሞ የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ቢልኢ አህመድ ናቸው።
“ተቋማዊ ተልዕኮዎችን ለማሳካት በአጭር፣ መካከለኛና ረጅም ጊዜ የተለያዩ ኮርሶችን በመስጠት ብቁ አመራሮችን ለማፍራት የሚያስችለን መሆኑን ተረድተናል” ሲሉም አክለዋል ።
በግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኩ የአፋር ክልል የፀጥታ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።