ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል ለመጅሊስ ምርጫ የምርጫ ቁሳቁስ ዝግጅት ተደርጓል

ሀዋሳ፤ ነሐሴ 7/2017 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ለመጅሊስ ምርጫ የሚውል ቁሳቁስ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ አስታወቀ።

ከነሐሴ 9 እስከ 11 ቀን 2017 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከወረዳ እስከ ፌደራል የመጅሊስ ምርጫ የሚካሄድ መሆኑን የወጣው መርሃ ግብር ያመላክታል።

በምርጫ ሂደቱ ህዝበ ሙስሊሙ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በአግባቡ መስራት ይችላሉ የሚላቸውን መብቱን ተጠቅሞ እንዲመርጥ ጥሪ ቀርቧል።

የሲዳማ ክልልን የምርጫ ዝግጅት በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ሃጂ ኢስማኤል ሲራጅ፤ በክልሉ በ44 መዋቅሮች በሚገኙ 483 መስጂዶች የመራጮች ምዝገባ ተጠናቆ የምርጫ ቁሶች ወደ መስጂዶች መግባታቸውን ገልጸዋል።

የምርጫ ሂደቱ ፍትሃዊ፣ አሳታፊ፣ አካታችና በቴክኖሎጂ የተደገፈ በመሆኑ የምርጫ ካርድ የወሰዱ ሁሉም በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ይሰሩልኛል ያሏቸውን በመምረጥ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ከነሀሴ 9 እስከ 11 ቀን 2017 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከወረዳ እስከ ፌደራል የመጅሊስ ምርጫ በመስጂዶች እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም