በተሐድሶ ሂደት ያለፉ የቀድሞ ታጣቂዎች የተቋማቱ አሰራር በሚፈቅደው መሰረት ወደ ቀደመ ስራቸው ይመለሳሉ፤ ጥቅማ ጥቅም ይከበራል− የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በተሐድሶ ሂደት ያለፉ የቀድሞ ታጣቂዎች የተቋማቱ አሰራር በሚፈቅደው መሰረት ወደ ቀደመ ስራቸው ይመለሳሉ፤ ጥቅማ ጥቅም ይከበራል− የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2017 (ኢዜአ)፡-በተሐድሶ ሂደት ያለፉ የቀድሞ ታጣቂዎች የየተቋማቱ አሰራር በሚፈቅደው መሰረት ወደ ቀደመ ስራቸው እንዲሚመለሱ እና ጥቅማ ጥቅም እንደሚከበርላቸው የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ ገለጹ፡፡
የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ በተሐድሶ ሂደት ያለፉ የቀድሞ ታጣቂዎች የየተቋማቱ አሰራር በሚፈቅደው መሰረት ወደ ቀደመ ስራቸው እንዲሚመለሱ እና ጥቅማ ጥቅም እንደሚከበርላቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን በመወከል በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ግዳጃቸውን በመወጣት ላይ ከነበሩ የሰራዊት አባላት መካከል ከተሰጣቸው ተልዕኮ በመውጣትና የቀድሞ ሕወሃትን በመቀላቀል በግጭቱ የተሳተፉ መኖራቸውን አመልክተዋል።
ኮሚሽኑ በግጭቱ የተሳተፉ የቀድሞ ታጣቂዎች በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሰረት መልሶ ለማቋቋም እንዲቻል መረጃቸውን ማደራጀቱን ጠቅሰው፤ የተሐድሶ ሥልጠና እየተጠባበቁ እንደሚገኙም አብራርተዋል።
በሱዳን ድንበር አካባቢ የሚገኙ የቀድሞ ታጣቂዎች በኮሚሽኑ አሰራር መሰረት ሥልጠና እንደሚወስዱና የማቋቋም ሥራ እንደሚከናወን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ ጠቁመዋል፡፡
የቀድሞ ታጣቂዎቹ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወቅት ከተባበሩት መንግስታት ሲሰጣቸው የነበረው የድጎማ ገንዘብ በመከላከያ ሰራዊት አሠራር መሰረት ተይዞባቸው መቆየቱን ጠቁመዋል።
እነዚህ የቀድሞ ታጣቂዎች የኮሚሽኑ የተሐድሶ አሰራር ሂደት እስካሟሉ ድረስ ገንዘቡ እንደሚከፈላቸውና ጥቅማ ጥቅም እንደሚከበርላቸው ተናግረዋል።
ከፕሪቶርያው ስምምነት በኋላ የጸጥታ አካላትን ጨምሮ ማንኛውም የመንግስት ሠራተኛ ወደ ስራው ሲመለስ በተቋሞቻቸው አሰራርና መርህ መሰረት ጥቅማ ጥቅም ይከበራል ብለዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹን በተሐድሶ ሂደቱ እንዲያልፍ በማድረግ ህጋዊ ዲጂታል መታወቂያ እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ ኮሚሽኑ ተቋማቱም ጥቅማ ጥቅም እንዲያስከብሩ የማድረግ ሃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ቀደም ብለው በመከላከያ ሰራዊት የከፍተኛ አመራር አባል የነበሩና ወደ ሰላም የመጡ በተሐድሶ ሂደቱ ካለፉ በኋላ ጥቅማ ጥቅም እንደሚከበር ጠቁመው፤ ይህም የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ አሰራሩ እንደሚያዝና ኮሚሽኑም ይህን እንደሚያስፈጽም አብራርተዋል።
የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን 65ሺህ 500 የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሃድሶ ሂደት በማሳለፍ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረጉን ኢዜአ ትናንት በሰራው የዜና ዘገባ መግለጹ ይታወቃል፡፡
ለዚህም የፌዴራል መንግሥት የቀድሞ ታጣቂዎችን ለማሰልጠን፤ ለስልጠና ማዕከላት ጥገና፣ ለምግብ፣ ለአልባሳት እንዲሁም ለተለያዩ ጉዳዮች እስከ አሁን አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ማውጣቱ ተጠቁሟል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹን ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ ለእያንዳንዳቸው 90 ሺህ 400 ብር መሰጠቱን እና በአጠቃላይ ከአጋር አካላት አምስት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡