የፀሐይ ኃይልን ለመስኖ ልማት ማስፋፊያ፤የከተማና የገጠር ኢኮኖሚን ማስተሳሰሪያ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የፀሐይ ኃይልን ለመስኖ ልማት ማስፋፊያ፤የከተማና የገጠር ኢኮኖሚን ማስተሳሰሪያ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 7/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የፀሐይ ኃይልን ከብርሃንና ከምግብ ማብሰያነት ባለፈ ለመስኖ ልማት ማስፋፊያ፣ የከተማና የገጠር ኢኮኖሚን ማስተሳሰሪያ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) ገለጹ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት በፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ የሶላር ሚኒግሪድና የሶላር ፓርክ ፕሮጀክት ግንባታ ማስጀመሪያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የሁለትዮሽ የትብብር ስምምነቱ በፀሐይ ኃይል ፓርክና የሶላር ሚኒ ግሪድ የኃይል ማመንጫ፣ በመስኖና መጠጥ ውሃ አቅርቦትን የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ትብብር ዕድሎችን የሚያመቻች መሆኑ ተገልጿል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ የፀሐይ ኃይል የማመንጨት ከፍተኛ አቅም ቢኖራትም በእስካሁኑ ሂደት ጥቅም ላይ ያዋለችው ከ10 ሜጋ ዋት በታች ነው ብለዋል።
ከዋና የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ርቀው የሚገኙ መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው እየተተገበሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ከዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር የሚደረገው የትብብር ስምምነትም የኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ለማስፋት ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ መሆኑን አስታውቀዋል።
በስምምነቱም ግብርናን በማዘመን በፀሐይ ኃይል የሚሰራ ከአየር ብክለት የጸዳ ቴክኖሎጂ ትግበራን ጨምሮ ልዩ ልዩ የአቅም ግንባታና የፀሐይ ኃይል ልማት ተደራሽነትን ለማስፋፋት እንደሚረዳ አንስተዋል።
የ400 ሜጋ ዋት የፀሐይ ፓርክ እና የፀሐይ ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት ውጥኖችን በማሳካት የኢትዮጵያን የገጠር ኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ማስፋት የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል።
ኢትዮጵያ ለዘላቂ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ምቹ ምኅዳር በመፍጠር ሁሉም ዜጎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አስቻይ ሁኔታ እየፈጠረች እንደምትገኝ አብራርተዋል።
ሀገሪቱን ቀጣናዊ የኃይል ማዕከል ለማድረግም እየተሠራ ነው ያሉት ዴኤታው፥ የፀሐይ ኃይልም ከብርሃንና ከምግብ ማብሰያነት የተሻገረ ሚና እንዲኖረው ተጨባጭ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
በዚህም በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የመስኖ አውታሮችን በመዘርጋት የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ ሃብትን ጥቅም ላይ የማዋልና የከተማና የገጠር ኢኮኖሚን የማስተሳሰር ስራ በመከናወን ላይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሀይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል የታደለች ናት ያሉት የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት ዋና ዳይሬክተር አሺሽ ከሀና፥ ስምምነቱ በኃይል ተደራሽነት የተመሰረተ የግብርና ምርታማነትን የሚያካትት መሆኑን ገልጸዋል።
በስምምነቱ መሰረት 400 ሜጋ ዋት የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክትን ተግባራዊ ለማድረግ ግልጽና ዓለም አቀፍ ጨረታን የተከተለ ልማት ተግባራዊ ለማድረግ ድጋፍ እንደሚደረግ አንስተዋል።
የዓለም አቀፍ የጸሀይ ኃይል ጥምረት ኢትዮጵያን ጨምሮ 124 አባል ሀገራትን በማቀፍ የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ ልማትን ለማስፋፋት እየሰራ የሚገኝ ዓለም አቀፍ ተቋም መሆኑ ይታወቃል።