ቀጥታ፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና የኮሪደር ልማት ስኬት የላቀ የፕሮጀክት አመራርና የሥራ ባህል ለውጥ ማሳያ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2017 (ኢዜአ)፡-የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና የኮሪደር ልማት ስኬት የመንግሥት የላቀ የፕሮጀክት አመራር፣ የህዝብ ተሳትፎና የሥራ ባህል ለውጥ  ማሳያ መሆናቸውን የከተማ መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት ገለጹ። 

ሚኒስትር ዴኤታው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሥራ ባህል እየተቀየረ፣ የፕሮጀክት አመራርና ክትትል ውጤታማ እየሆነ መጥቷል።      

በኢትዮጵያ ለውጡን ተከትሎ ተግባራዊ በሆነው የልማት ፖሊሲ ሪፎርም መሰረት ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን የመጨረስ ባህል እየተገነባ መሆኑንም አንስተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመንግሥትና በሕዝብ የጋራ ርብርብ ለውጤት መብቃቱን ገልጸው ይህም ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ከማጠናቀቅ አኳያ ከፍተኛ ለውጥ ለመምጣቱ ማሳያ ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት በበርካታ የሀገሪቱ ከተሞች እየተከናወነ እንደሚገኝና በዚህ ረገድም አስደማሚ ውጤት መታየቱን አስታውቀዋል።   

በዚህም የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከፍ ያደረጉ ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን አስረድተዋል።    

የአመራር የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እየተጠናከረ መምጣቱ ፕሮጀክቶች ባጠረ ጊዜ እንዲጠናቀቁ ማስቻሉን ነው አቶ የትምጌታ ያነሱት።  

ቀን ከሌሊት የመሥራት ባህል እየዳበረ መምጣቱ ፕሮጀክቶች የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖራቸው ምክንያት መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም የተገኘውን ውጤት ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አሰራሮች እየተዘረጉ ነው።  

ለዚህም ብቁ ባለሙያዎች ማፍራትና የተቋማትን የማስፈጸም አቅም ለማጠናከር ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም