ህዝበ ሙስሊሙ በሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝበ ሙስሊሙ በሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2017 (ኢዜአ)፡-ህዝበ ሙስሊሙ ከነሐሴ 9 ጀምሮ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ጥሪ አቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ ምርጫውን ማካሔድ የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን አስታውቋል፡፡
የምርጫ አስፈጻሚ ቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አብዱልዋሲዕ የሱፍ(ዶ/ር) እንደተናገሩት የኡለማ፣ የምሁራን፣ የወጣቶች፣ የሴቶች እና የሠራተኛ ማኅበረሰብን የሚወክሉ ተመራጮች ምርጫ ከነሐሴ 9-11 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።
ምርጫውን ግልፅ፣ አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ምርጫው ህዝበ ሙስሊሙን በቅንነትና በታማኝነት የሚያገለግሉ አመራሮች ወደ ኃላፊነት የሚመጡበት ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ለምርጫ የተመዘገበ ሁሉም ህዝበ ሙስሊም በተጠቀሱት ቀናት በነቂስ ወጥቶ ድምጹን እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡