በሚዛን አማን ከተማ የተራቆተ አካባቢን አረንጓዴ በማልበስ ለቁንዶ በርበሬ ልማት እየዋለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሚዛን አማን ከተማ የተራቆተ አካባቢን አረንጓዴ በማልበስ ለቁንዶ በርበሬ ልማት እየዋለ ነው

ሚዛን አማን ፤ ነሐሴ 7/2017 (ኢዜአ)፡- በሚዛን አማን ከተማ የተራቆተ አካባቢን አረንጓዴ በማልበስ ለቁንዶ በርበሬ ልማት እየዋለ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።
በከተማዋ የአረንጓዴ አሻራ ልማት በአርሶ አደሮች ጓሮ፣ በተቋማት ግቢ እና በመንግስት የወል መሬቶች ላይ ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲከናወን ቆይቷል።
ከተማ አስተዳደሩ በሚዛን አማን ከተማ ካሉ የወል መሬቶች መካከል የድንጋይ ማዕድን የሚመረትበት የአማን ቀበሌን ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር አረንጓዴ የማልበስ ስራ ሲያከናውን ቆይቷል።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ኢንጂነር ሰሎሞን ሌዊ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀግብር የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ከማድረግ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በኩታገጠም ለማልማት ማስቻሉን ተናግረዋል።
ለአብነትም ቀደም ሲል ለከተማዋ የልማት ሥራ ድንጋይ ለማውጣት በሚደረግ ቁፋሮ ከጥቅም ውጭ ሆኖ የነበረው በአማን ቀበሌ የጋቡቃ መንደርን በአረንጓዴ አሻራ መልሶ በማልማት ቁንዶ በርበሬ መተከሉን ጠቅሰዋል።
ይህም አካባቢውን አረንጓዴ ከማልበስ ባለፈ ከቁንዶ በርበሬ ልማት ህብረተሰቡ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ አስችሏል ብለዋል።
የተራቆቱ ቦታዎች በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ችግኝ ከመትከል ባለፈ ከሰውና ከእንስሳት ንኪኪ ነጻ መደረጋቸው ውጤት አስገኝቷል ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምስራቅ አስናቀ ናቸው።
የአረንጓዴ ልማት ሥራውን በማጠናከር ለቁንዶ በርበሬ ቅመም ድጋፍ እንዲሆን የግራቪሊያ ዛፎች አብረው እንዲተከሉ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት ከተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች ልምድ በመውስድ በተራቆቱ አካባቢዎች ችግኝ እየተከሉ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ አቶ ትዕዛዙ ኬንጫ ናቸው።
የተተከሉ ችግኞች ጸድቀው ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውሉ ተገቢ እንክብካቤ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ልማት የተራቆቱ ቦታዎች መልሰው ማገገማቸው የሕብረተሰቡን ችግኝ የመትከል ተነሳሽነት እንዳሳደገው የገለጸው ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ተዘራ ጥላሁን ነው።
ችግኞችን ከመትከል ባሻገር መንከባከብ ያለውን ውጤት በከተማው ጋቡቃ አካባቢ የተተከለው የግራቪላ ዛፍ ማሳያ መሆኑን ጠቅስዋል።
በሚዛን አማን ከተማ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ፍራፍሬን ጨምሮ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በስፋት እየተተከሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።