ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ማህበራዊ ችግር ከማቃለል ባለፈ ኢትዮጵያዊ እሴት እንዲጎለብት እያደረገ ነው

አሶሳ፤ ነሐሴ 07/2017 (ኢዜአ)፦ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ማህበራዊ ችግሮች ከማቃለል ባለፈ ኢትዮጵያዊ እሴት እንዲጎለብት እያደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስ አስታወቁ።

የግብርና ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር በአሶሳ ከተማ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን አከናውነዋል።


 

ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ በአሶሳ ከተማ የአምስት አቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታ እና እድሳት ስራ ያስጀመሩ ሲሆን  ለ1 ሺህ 700 ህፃናትም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስ በወቅቱ እንደገለፁት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ችግሮች ከማቃለል ባለፈ  ኢትዮጵያዊ እሴቶች እንዲጎለብቱ እያደረገ ነው።

ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ 35 ቤቶችን እየገነቡ መሆኑን ጠቅሰው በአሶሳ ከተማ የአምስት አቅመ ደካማ ቤቶችን ግንባታ ለማከናወን ወደ ተግባር ገብተናል ብለዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የአቅመ ደካሞችን ህይወት ከማሻሻል ባለፈ  ለተማሪዎች የመማሪያ  ቁሳቁስ  በማሟላት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ  ማገዙን ተናግረዋል።


 

የሚኒስቴሩ አጋሮችና ተጠሪ ተቋማቱ በየጊዜው ለሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተባባሪ በመሆናቸው ሚኒስቴር ዴኤታው አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኮሚሽኑ እንደ ሀገር የተጀመረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመደገፍ በሸገር እና አሶሳ ከተማ የቤት እድሳት እና ግንባታ እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።


 

ኮሚሽኑ ቤቶቹን በተያዘላቸው ጊዜ አጠናቆ ለማስረከብ ዝግጁ መሆኑን ገልፀው፥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊ ኑሮ የሚያቃልል በመሆኑ በሁሉም ቦታዎች ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል።


 

የሚኒስቴሩ እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች የተለያዩ የልማት ስራዎችንም የተመለከቱ ሲሆን የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም