በክልሉ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እና ጥራትን ለማሳደግ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እና ጥራትን ለማሳደግ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል
ሐረር፤ ነሐሴ 7/2017 (ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እና ጥራትን ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸው ተገለጸ።
የጤና ሚኒስቴር ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በ96 ሚሊዮን ወጪ ያስገነባው የጤና ምርመራ ላቦራቶሪ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪና የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን እንደተናገሩት፤ በክልሉ የጤናው ዘርፍ አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት በማሳደግ ረገድ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።
በዚህም በሽታን አስቀድሞ በመከላከልና አክሞ በማዳን በኩል አመርቂ ውጤት እያሳየ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በእለቱ የተመረቀው ሪጅናል ላቦራቶሪ የጤና አገልግሎት ደረጃን የሚያሳድግና ከክልሉ ባለፈ የአጎራባች አካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በዘመናዊ መልኩ የተገነባው ሪጅናል ላቦራቶሪው የምርመራ አቅምን በማሳደግ የክልሉን የጤና ዘርፍ ለማጎልበት እንደሚያግዝ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሪጅናል ላቦራቶሪው በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እንዲሰጥ ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ ባለፉት ሰባት ዓመታት 28 ላቦራቶሪዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
ይህም ተግባር መንግስት ለጤናው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ አመልክተዋል።
ውስብስብ የጤና ምርመራ ማድረግ የሚችሉት የላብራቶሪ ማዕከላቱ የጤናውን ዘርፍ ከማጎልበት አንጻር ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታሉ ነው ያሉት።
መንግስት ጥራት፣ ብቃትና ቀጣይነት ያለው የላብራቶሪ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በመመደብ እየሰራ ይገኛል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ ናቸው።
ላብራቶሪዎቹም ዘመኑን የዋጁና ቴክኖሎጂዎችን የያዙ በመሆናቸው በጤና ምርመራ ስራ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።
የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብዲ አሚን በበኩላቸው ቀደም ሲል አገልግሎቱን በሚፈልጉ ዜጎች ላይ ሲደርስ የቆየውን እንግልትና ወጪን ያስቀራል ብለዋል።
በምረቃው ስነ ስርዓት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር፣ ሚኒስትር ዴዔታዎች፣ የክልል ጤና ቢሮ ሃላፊዎች፣ከፍተኛ የክልሉ ባለስልጣናት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡