የፀሐይ ኃይልን ጨምሮ እምቅ የኃይል አማራጮችን ጥቅም ላይ ለማዋል ትኩረት ተሰጥቷል - ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
የፀሐይ ኃይልን ጨምሮ እምቅ የኃይል አማራጮችን ጥቅም ላይ ለማዋል ትኩረት ተሰጥቷል - ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የፀሐይ ኃይልን ጨምሮ በኃይል አማራጭ ያላትን ዕምቅ አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል በትኩረት እየሰራች መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ(ዶ/ር) ገለጹ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት በፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ የሶላር ሚኒግሪድና የሶላር ፓርክ ፕሮጀክት ግንባታ ማስጀመሪያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የሁለትዮሽ የትብብር ስምምነቱ በዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ልማት ትግበራ ሂደት የፀሐይ ፓርክና የሶላር ሚኒ ግሪድ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች፣ የመስኖና መጠጥ ውሃ አቅርቦትን በማሳደግ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ትብብር ዕድሎችን ማመቻቸት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
ሚኒስትር ዴኤታው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ አስተማማኝ፣ ዘላቂና ተመጣጣኝ የኃይል አቅርቦት የሀገርን ሁለንተናዊ ልማትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያ የፀሐይ ኃይልን ጨምሮ እምቅ የኃይል አማራጮችን ጥቅም ላይ ለማዋል በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝ አስታውቀዋል።
የፀሐይ ኃይል አማራጭ ለሀገር ዕድገት ትልቅ ሚና ይጫወታል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ለዚህም ከዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረትና ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።
የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት ዘላቂ የልማትን ግቦችን ለማሳካት ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ጥምረቱ የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂዎችን፣ ተቋማዊ አቅም ግንባታንና ለታዳሽ ኃይል መስፋፋት ምቹ የሕግ ማዕቀፍ መፍጠር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ እገዛ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ከዋናው ኃይል ቋት ወደ እያንዳንዱ መንደር የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ በትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።
የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት ዋና ዳይሬክተር አሺሽ ከሀና፥ ኢትዮጵያ በታዳሽ የኃይል አማራጭ ልማት መስክ ያላትን ዓለም አቀፍ ትብብር በማስፋት ዕድገቷን ማስቀጠል የሚያስችል ስኬታማ ስራ በማከናወን ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በቀጣይም የፀሐይ ኃይል አማራጭ ልማቷን ለማስፋት በምታደርገው ጥረት ጥምረቱ በተለያዩ መስኮች ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።