የቻን የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2017 (ኢዜአ)፡- በስምንተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና (ቻን) የ11ኛ ቀን ውሎ የምድብ ሁለት አራተኛ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ማዳጋስካር ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ከቀኑ 11 ሰዓት በቤንጃሚን ምካፓ ብሄራዊ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በሁለት የምድብ ጨዋታዎቿ አንድ ነጥብ ያገኘችው ማዳጋስካር አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። 

ተጋጣሚዋ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሁለት ሽንፈት አስተናግዳ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አምስተኛ ደረጃን ይዛለች።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ሰባት ጊዜ እርስ በእርስ ተገናኝተው ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሶስት ጊዜ ስታሸንፍ ማዳጋስካር ሁለት ጊዜ ድል ቀንቷታል።  ሁለት ጊዜ አቻ ወጥተዋል።

በጨዋታዎቹ ሁለቱም ሀገራት በተመሳሳይ 11 ግቦችን አስቆጥረዋል። 

ቡድኖቹ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በምድቡ ያሉ የሌሎች ቡድኖች ውጤት ይጠብቃሉ። 

በዚሁ ምድብ ምሽት 1 ሰዓት ሞሪታኒያ ከቡርኪናፋሶ በቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በምድቡ ሞሪታኒያ በአራት ነጥብ ሁለተኛ፣ ቡርኪናፋሶ በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ሞሪታኒያ ካሸነፈች ወይም አቻ ከወጣች ቀጥታ ወደ ሩብ ፍጻሜው ትገባለች። ቡርኪናፋሶ ወደ ሩብ ፍጻሜው ለማለፍ የግዴታ ማሸነፍ አለባት። 

ሀገራቱ ከዚህ ቀደም 10 ጊዜ ተገናኝተው ቡርኪናፋሶ 6 ጊዜ ድል ሲቀናት ሞሪታኒያ 1 ጊዜ አሸንፋለች። 3 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

ምድብ ሁለትን በዘጠኝ ነጥብ የምትመራው ታንዛንያ ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፏ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም