ፒኤስጂ እና ቶተንሃም ሆትስፐርስ የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ለማንሳት ይጫወታሉ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2017(ኢዜአ)፦ የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በፈረንሳዩ ፒኤስጂ እና በእንግሊዙ ቶተንሃም ሆትስፐርስ መካከል ዛሬ ይደረጋል።

ጨዋታው ምሽት 4 ሰዓት ላይ በጣልያኑ ዩዲኒዜ ክለብ ሜዳ ብሉኢነርጂ ስታዲየም ይካሄዳል።

ፒኤስጂ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ የዩሮፓ ሊግ ሊግ አሸናፊ መሆናቸውን ተከትሎ ለፍጻሜው ጨዋታ ደርሰዋል።

የፈረንሳዩ ቡድን በሻምፒዮንስ ሊጉ ፍጻሜ ኢንተር ሚላንን 5 ለ 0 በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ማንሳቱ የሚታወስ ነው።

በስፔናዊው ሉዊስ ኤነሪኬ የሚመራው ቡድን የፈረንሳይ ሊግ 1፣ የፈረንሳይ ጥሎ ማለፍ እና የፈረንሳይ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫዎችንም አንስቷል።

ፒኤስጂ በዘንድሮው የፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ ለፍጻሜ ደርሶ በቼልሲ ያልተጠበቀ የ3 ለ 0 ሽንፈት ማስተናገዱ የሚታወስ ነው።

በአንጻሩ እ.አ.አ በ2024/25 በአንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ቶተንሃም ሆትስፐርስ በዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ ማንችስተር ዩናይትድ በማሸነፍ የቀጣዩ ዓመት የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን አግኝቷል። 

የሰሜን ለንደኑ ቡድን በሊጉ መጥፎ የሚባል የውድድር ጊዜ አሳልፏል። 

ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከ41 ዓመት በኋላ ክለቡን ለአውሮፓ ክብር ያበቁትን አሰልጣኝ አንጌ ፖስትኮግሉን ማሰናበቱ ያልተጠበቀ ውሳኔ ነበር።

በምትካቸው የብሬንትፎርድ አሰልጣኝ የነበሩትን ቶማስ ፍራንክን ሾሟል።  

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ በፊት እርስ በእርስ የተገናኙት እ.አ.አ 2006 የቅድመ ውድድር የአቋም መለኪያ ሲሆን ቶተንሃም ሆትስፐርስ 3 ለ 0 አሸንፏል።

ቡድኖቹ በውድድር ጨዋታዎች ላይ ከዚህ ቀደም ተገናኝተው አያውቁም። 

ፒኤስጂ ለአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ሲጫወት የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን እ.አ.አ 1996 ከጁቬንቱስ ጋር ተጫውቶ ሽንፈት አጋጥሞታል።

ቶተንሃም ሆትስፐር ለውድድሩ ፍጻሜ ሲቀርብ የአሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ ነው። 

የፈረንሳዩ ክለብ ካለበት ድንቅ ብቃት አንጻር ጨዋታውን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝቷል። 

ዝቅተኛ የማሸነፍ ግምት ያገኘው ቶተንሃም ሆትስፐርስ በእግር ኳስ ሁልጊዜ የሚባለውን ያልተጠበቀ ድል ሊያስመዘግብ ይችላል።

የ37 ዓመቱ ፓርቹጋላዊ ጆአኦ ፒንሄሮ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም