የኢትዮጵያ ፍትሃዊ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ የሁላችንም ትኩረት ሆኖ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፍትሃዊ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ የሁላችንም ትኩረት ሆኖ ይቀጥላል
ባሕር ዳር፤ ነሐሴ 7/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፍትሃዊና በየትኛውም መመዘኛ ትክክለኛ የሆነው የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ከባሕር ካላት ቅርበትና ከሕዝብ ብዛቷ አንፃር የባህር በር ሊኖራት ግድ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአንድ ወቅት የባህር በር ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ በሌላ ጊዜ ደግሞ የባሕር በር በማጣት የተቆለፈባት ሀገር ሆና ለብዙ ችግሮች እየተዳረገች ትገኛለች።
ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ በአቅራቢያቸው ባሕር እያለና በርካታ አገራት እየተጠቀሙበት የበይ ተመልካች መሆን የለባትም የሚል ፅኑ አቋም በመያዝ የባሕር በር ለማግኘት መንግስት ያላሰለሰ የዲፕሎማሲ ጥረት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ተደጋጋሚ ማብራሪያዎችን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ ቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ መሆኑን አጽኖት ሰጥተዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በሰላማዊና በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር ለማግኘት የዲፕሎማሲ ጥረቷን አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ካነጋገራቸው የምክር ቤት አባላት መካከል ወይዘሮ ፋጡማ ይማም፣ እናትነሽ በዛብህ (ዶ/ር) እና አቶ አሊ ይማም ኢትዮጵያ ከባሕር ካላት ቅርበትና ከህዝብ ብዛቷ አንፃር የባህር በር ሊኖራት ግድ ይላል ሲሉ ተናግረዋል።
የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ መንግስት ጉዳዩን ዓለም አቀፍ አጀንዳ አድርጎ እየሰራ በመሆኑ አድንቀው ኢትዮጵያዊያንም ያለልዩነት በጋራ የሚቆሙበት ጉዳይ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም ለኢትዮጵያ ህጋዊ፣ ፍትሃዊና በየትኛውም መመዘኛ ትክክለኛ የሆነው የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እስከሚያገኝ የሁላችንም ጥያቄ ሆኖ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
ለዚሁ ጉዳይ በሰጥቶ መቀበል መርህ ሕዝብና መንግስት ለማስፈጸም የትኩረት አጀንዳ ያደረጉበት ጉዳይ ነው።
ይህም ሰፊ የሕዝብ ቁጥርና ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ላለች ሀገር የባሕር በር ጥያቄ በታሪክም ሆነ በዓለም አቀፍ ህጎች መሰረታዊ ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የምክር ቤቱ አባላት መካከል ወይዘሮ ፋጡማ ይማም፤ በሰጥቶ መቀበል መርህ የባሕር በር ጥያቄው እውን እንዲሆን የሁላችንንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።
የባሕር በር ጥያቄው ትውልድ ተሻጋሪ የመልማት ጥያቄን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ወቅቱን የጠበቀ አጀንዳ እንደሆነ ገልፀዋል።
የለውጡ መንግስት የሕዝብን ጥያቄ አጀንዳ ሆኖ ማቅረቡ የኢትዮጵያን የባሕር በር ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የባሕር በር ጥያቄው እንዲሳካም የሕዳሴ ግድቡን በላቀ ትብብር እንደገነባነው ሁሉ በጋራ ጥረት መስራት ይጠይቃል ያሉት ደግሞ እናትነሽ በዛብህ (ዶ/ር) ናቸው።
ጥያቄው የተፈጥሮ ሃብትን የመጠቀም መብትን መነሻ ያደረገ ፍትሃዊነትን የተላበሰ መሆኑን አንስተዋል።
አቶ አሊ ይማም በበኩላቸው እንዳመለከቱት፤ በዚህ ዘመን የባሕር በር አልባ ሆኖ መኖር አስቸጋሪ ነው።
አሁን ላይ መንግስት የባሕር በር በሰላማዊ አማራጭ ለማግኘት እየሄደበት ያለው ርቀት የሚደነቅና የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እንደሆነ ተናግረዋል።
ለጥያቄው ምላሽ ለማግኘት የህግም የሞራል መብት መኖሩን ጠቅሰው፤ እነሱም የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።