ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል አደጋን በራስ አቅም ለመቋቋም የተጀመሩ ስራዎች ውጤት እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 7/2017(ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራት ውጤት እያስገኙ መሆኑን ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በሚል እንቅስቃሴ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትልቅ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ሰሞኑን ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን ሀገራዊ ግብን የሚያሳኩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የገለጸ ሲሆን በዚህ ሂደትም በርካታ ክልሎች መደበኛ የሰብዓዊ ድጋፍን በራሳቸው ማሟላት መቻላቸውን ጠቁሟል።

ክልሎች ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችላቸውን የምርት አቅርቦት ለመሸፈን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 100 ሺህ ሔክታር መሬት መልማቱን ኮሚሽኑ አመልክቷል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም ከገዳ ስርዓት በመነጨው ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ የተሰኘ የህዝቡ ነባር የመረዳጃ ስርዓትን ህጋዊ መሰረት አስይዞ እየተገበረ ሲሆን ውጤት እያስገኘ መሆኑን የክልሉ ቡሳ ጎኖፋ ገልጿል።

የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሀይሉ በነበራቸው ቆይታ በዚሁ የእርስ በርስ የመረዳዳት ሥርዓት አማካኝነት የክልሉ ህዝብ አደጋ ሲያጋጥመው በሚችለው ሁሉ እየተደጋገፈ ይገኛል ብለዋል።

የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋ ከመድረሱ በፊት የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው ሊከሰት በሚችለው አደጋ ዙሪያም ህብረተሰቡን የማንቃት ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ አልፎ አደጋ ካጋጠመም ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶችን ያካተተ ኮሚቴ ተቋቁሞ የተለያየ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ ስርዓት ህብረተሰቡ አደጋ የመከላከል አቅሙን እንዲያጎለብት ማስቻል፣ በአደጋው የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ እና ለድጋፍ የሚውል ሀብት የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

እስካሁን በተሰራው ስራም የክልሉ መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት አደጋን በመቋቋም ረገድ በተሰራው ስራ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

በዋናነት የክልሉ መንግስት የተለያዩ የልማት ኢንሼቲቮችን ቀርጾ ውጤታማ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ገልጸው የሚከናወኑ የልማት ስራዎችም ለአደጋ የማይበገር ህብረተሰብ መገንባት መሆኑን አክለዋል።

ለአብነትም የክልሉ መንግስት ለሰብዓዊ ድጋፍ እንዲውል በቡሳ ጎኖፋ አማካኝንት ካለማው የእርሻ መሬት ከ9 ሺህ 369 ኩንታል በላይ ምርት ማምረት መቻሉን በማሳያነት አንስተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም በክልሉ ስድስት ዞኖች ውስጥ ለሰብዓዊ ድጋፍ የተለየ 7 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች እየለማ መሆኑንም አመልክተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ህብረተሰቡ ችግር ሲያጋጥም ወደ ውጪ ከመመልከት ይልቅ የእርስ በርስ የመረዳዳት ባህሉን የበለጠ እንዲያጠናክር ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ በእርስ በርስ የመረዳዳት ባህልን መሰረት ተደርጎ በክልሉ በአዋጅ የተቋቋመ ሥርዓት ሲሆን፤ ከ27 ሚሊዮን በላይ አባላት እንዳሉትና ከአባላቱ የሚሰበሰበው መዋጮም የሥርዓቱ ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም