ከክረምቱ ጋር ተያይዞ ሊያጋጥም የሚችለውን የጎርፍ አደጋ የመከላከሉ ተግባር ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከክረምቱ ጋር ተያይዞ ሊያጋጥም የሚችለውን የጎርፍ አደጋ የመከላከሉ ተግባር ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው

ጅግጅጋ፣ ነሐሴ 7/2017 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል ከክረምቱ ወራት ጋር ተያይዞ ሊያጋጥም የሚችለውን የጎርፍ አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
በክረምት ወራት ከወንዞች መሙላትና ተዳፋታማ የሆነ የመሬት አቀማመጥ ባላቸው አካባቢዎች ደግሞ ደራሽ የጎርፍ አደጋ ይከሰታል።
ይኸንኑ ስጋት ከግምት በማስገባት የዋቤና ገናሌ ወንዞች አቋርጠው የሚፈሱበት የሶማሌ ክልል ሊያጋጥም የሚችለውን አደጋ ስጋት ለመከላከል የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸው ተገልጿል።
የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ አስተዳደር አስተባባሪ አቶ አብዲቃድር ሙሁመድ ለኢዜአ እንደገለጹት በክረምቱ ወቅት ሊያጋጥም የሚችል የጎርፍ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።
በዚህም ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ነዋሪዎችን ወደ ተሻለ ቦታ የማስፈርና አደጋ እንዳለባቸው የተለዩ አካባቢዎች ላይ ደግሞ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
በበጋው ወራት የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች የዚሁ ጥረት አካል መሆናቸውን ያነሱት አስተባባሪው የለሙ ተፋሰሶችን ደግሞ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በችግኝ የመሸፈን ሥራዎችም እየተሰሩ ነው ብለዋል።
በተለይም የተጎዱ መሬቶች ላይ ችግኝ መትከል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በቋሚነት መሰራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ስራ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የህብረተሰቡን የስነ-ምግብ ስርዓት ማሻሻል ላይ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልጸው፤ በዚህ ረገድ ውሃ በመያዝ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ በሰፊው እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተያዘው ክረምትም በሚጥለው ዝናብ የሚከሰተውን የጎርፍ ስጋት በመከላከል ላይ ህብረተሰቡም የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በአግባቡ በመተግበር ራሱን መጠበቅ እንዳለበትም አቶ አብዲቃዲር አሳስበዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን ለመከላከል ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት ጋር በመተባበር መረጃዎችን ለህብረተሰቡ የሚሰጡ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልእክቶች እንደሚያስተላልፍ ገልጸው፤ መልዕክቶቹን በመከታተል የቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።