ቀጥታ፡

ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የማሕበረሰቡ እሴቶች ጎልተው እንዲወጡ እያስቻለ ነው

አሶሳ፤ ነሐሴ 7/2017 (ኢዜአ)፦ ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት  የማሕበረሰቡ እሴቶች  ጎልተው እንዲወጡ  የሚያደርግና የህሊና እርካታ የሚገኝበት መልካም ሥራ   መሆኑን የአገልግሎቱ ተሳታፊዎች ተናገሩ።

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ "የተደመረ የወጣቶች አቅም ለዘላቂ ልማት ግቦች" በሚል መሪ  ሀሳብ  የዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን   በአሶሳ ከተማ አክብሯል።


 

በዚህ  ወቅት  በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩ ወጣቶች  ያገኙትን መልካም ተሞክሮ አካፍለዋል። 

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሆሞሻ ወረዳ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ  የተሳተፈችው ወጣት ርቅያ መሀመድ በሰጠችው አስተያየት፤ በየአካባቢው  የሚደረግላቸው አቀባበል እና መስተንግዶ የማሕበረሰቡን መልካም እሴት ያየሁበት አጋጣሚ ነው ብላለች።

ይህም ወጣቶች የሀገር ፍቅር  እንዲኖራቸውና በሁሉም አካባቢዎች የማሕበረሰቡ እሴቶች ጎልተው እንዲወጡ የሚያደርግ መሆኑን ገልፃለች።

በአፋር፣ አማራ ክልል እና ሌሎች አካባቢዎች በደም ልገሳ፣ ችግኝ ተከላ እና ሌሎችም  የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ በመሳተፍ የተሳካ ጊዜ እንዳሳለፉ ተናግራለች።

ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶች ጋር እርስበርስ ተሞክሮ በመለዋወጥ፣ ስለሀገር በመመካከር እና የተቸገሩትን በመርዳት ማሳለፋቸውን ጠቅሳለች።


 

በትግራይ እና ሱማሌ ክልሎች የቆየው ሌላው በወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣት ሱዋር ማሳድ በበኩሉ፤  የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማሕበረሰቡን ዝቅ ብሎ በማገልገል የህሊና እርካታ የሚገኝበት መልካም ሥራ ነው ብሏል።

በሁሉም አካባቢዎች የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማከናወናቸውን  ገልፆ፤  በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ወጣቶች በስፋት ቢሰማሩ መልካም መሆኑን  ጠቁሟል።

ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶችን ለአንድ ዓላማ የሚያሰባስብ እና ለሕብረተሰቡ አለኝታ መሆናቸውን የሚያረጋግጡበት ነው ያለው ደግሞ  የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክርቤት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወጣቶች ምክርቤት ፕሬዚዳንት ወጣት መሀመድ መሀሙድ ነው።


 

ምክር ቤቱ ወጣቶች በሀገር ጉዳይ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቁሞ፤ ወጣቶች ክረምቱን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲያሳልፉ መልዕክት አስተላልፏል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ  የተከበረው  የዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን  በዓለም ለ25ኛ ጊዜ ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ22ኛ ጊዜ እንደሆነ ተመልክቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም