እጥረት የታየባቸው የመማሪያ እና የማስተማሪያ መጽሐፍት እየታተሙ ነው - ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
እጥረት የታየባቸው የመማሪያ እና የማስተማሪያ መጽሐፍት እየታተሙ ነው - ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2017(ኢዜአ)፡- እጥረት የታየባቸውን የመማሪያ እና ማስተማሪያ መጽሐፍት ለመቅረፍ በ20 ሚሊየን ዶላር ሕትመት እየተከናወነ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሁለት ዙር 43 ነጥብ 5 ሚሊየን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የመማሪያ ማስተማሪያ መጽሐፍት ታትመው ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ማሰራጨቱን ገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎም በሁለተኛ ደረጃ የመጽሐፍት ተማሪ ጥምርታ 1 ለ 1 መድረሱን በሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ዴስክ ኃላፊ ዛፉ አብርሃ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ከቅድመ አንደኛ እስከ 8ኛ ክፍል ሥርዓተ ትምህርቱን በባለቤትነት የሚመሩት ክልሎች መሆናቸውንና፤ መጽሐፍትን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር አብዛኛው ክልሎች አበረታች ተግባራት አከናውነዋል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ እና ሐረሪ ክልል አንደኛ ደረጃ የመጽሐፍ ተማሪ ጥመርታ 1 ለ 1 መድረሱን ገልጸው፤ በሌሎች ክልሎች ደግሞ 1 ለ 3 መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከቅድመ አንደኛ እስከ 8ኛ ክፍል እጥረት የታየባቸውን (እንግሊዝኛ፣ ሂሳብና አካባቢ ሳይንስ) የመማሪያ ማስተማሪያ መጽሐፍት እጥረት ለመቅረፍ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በ20 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ የመማሪያ ማስተማሪያ መጽሐፍት እየታተሙ ነው ብለዋል፡፡