በስምንተኛው የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒዮና(ቻን) ጨዋታ ሱዳን ናይጄሪያን አሸነፈች - ኢዜአ አማርኛ
በስምንተኛው የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒዮና(ቻን) ጨዋታ ሱዳን ናይጄሪያን አሸነፈች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2017(ኢዜአ)፦ በስምንተኛው የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒዮና (ቻን) የምድብ አራት ጨዋታ ሱዳን ናይጄሪያን ባልተጠበቀ ሁኔታ 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ረታለች።
ማምሻውን በቤንጃሚን ምካፓ ብሄራዊ ስታዲየም በተደረገው መርሃ ግብር የአማካይ ተጫዋቹ አብደል ራኦፍ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ዋሊልዲን ከድር በፍጹም ቅጣት እና የናይጄሪያው ሊኦናርድ ንጌንጌ በራሱ ግብ ላይ ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
በጨዋታው ሱዳን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወሰድባትም ለግብ የቀረቡ እድሎችን በመፍጠር ተሽላ ተገኝታለች።
ውጤቱን ተከትሎ ሱዳን ነጥቧን ወደ አራት ከፍ በማድረግ ተመሳሳይ ነጥብ ያላትን ሴኔጋልን በግብ ክፍያ በልጣ የምድቡ መሪ ሆናለች።
ሁለተኛውን ሽንፈቷን ያስናገደችው ናይጄሪያ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አራተኛ በመያዝ ከውድድሩ የተሰናበተች የመጀመሪያ ሀገር ሆናለች።
በዚሁ ምድብ ዛሬ በተደረገ ጨዋታ የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ሴኔጋል ከኮንጎ ብራዛቪል አንድ አቻ ተለያይታለች።
በመጨረሻው የምድብ መርሃ ግብር ሴኔጋል ከሱዳን፣ ናይጄሪያ ከኮንጎ ብራዛቪል ነሐሴ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።