ቀጥታ፡

በተለያዩ ሀገራት የሚገኘው የዳያስፖራ ማህበረሰብ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው አጀንዳዎችን ማዘጋጀት አለበት - ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2017(ኢዜአ)፡- የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ለወቅቱ የኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ መሆን የሚችሉ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው አጀንዳዎችን እንዲያዘጋጅ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በቅርቡ ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ እንደሚከናወን በሰጡት ማብራሪያ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አዲስ አበባ ከተማ እና የድሬዳዋ አሥተዳደርን ጨምሮ 11 ክልሎችን ጨርሶ ወደ በትግራይ ክልል ለማከናወን አጀንዳ ማሳባሰብ የሚያስችል ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ተመሳሳይ ሥራ እንደሚሠራ እና ከዚህ ጋር በተያያዘ ወደ ተግባር መገባቱን አንስተዋል፡፡

ከጊዜም ሆነ ከገንዘብ አቅም አኳያ ሁሉንም ሀገራት ማዳረስ ስለማይቻል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራው የሚከናወነው በበይነመረብ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር መወያየቱን አጀንዳዎችም እየቀረቡ መሆኑን ገልጸው፤ በተመሳሳይ በአውሮፓ፣ እስያ እና ትራንስ አትላንቲክ የበይነመረብ ግንኙነቶች ይደረጋሉ ነው ያሉት፡፡

በአንጻሩ ወደ ደቡብ አፍሪካ-ፕሪቶሪያ ኮሚሽነሮች ሂደው በአካል አጀንዳ መሰብሰብ የጀመሩባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የተረከቡትን አጀንዳ በቅርቡ ለኮሚሽኑ ምክር ቤት እንደሚያቀርቡ አመላክተዋል፡፡

በተመሳሳይ በዋሽንግተን ዲሲ ከፈረንጆቹ ነሐሴ 23 እስከ 31 ቀን 2025 እንዲሁም በመቀጠልም በካናዳ-ቶሮንቶ፣ ብሪታንያ-ለንደንና ስዊድን-ስቶክልም ኮሚሽነሮች በአካል እንደሚገኙ ነው የጠቆሙት፡፡

የኢትዮጰያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሀገራዊ አጀንዳ እንደሚሰበስብ በመገንዘብ፤ ከሕገ መንግሥቱ እና ከኢትዮጵያ ውጭ ለማንም ሳይወግን ሁሉንም ለማስተናገድ እንደሚሠራ በመገንዘብ ንቁ ተሳትፎ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዳያስፖራውን ጨምሮ ከሁሉም ወገን የሚሰበሰቡ 4ሺህ ገደማ አጀንዳዎች ላይ ምክክር ይደረጋል ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ መግባባት ላይ የሚደረስባቸው አጀንዳዎችም ለተግባሪ አካል ይቀርባሉ፤ መተግበሩንም ኮሚሽኑ ተከታትሎ ለሕዝብ ያሳውቃል ብለዋል፡፡

አጀንዳዎችንም በበይነመረብ፣ በድረገጽ፣ በፖስታ፣ በስልክ፣ በቤተሰብ አባላትና በጓደኞች በኩል ጭምር ማቅረብ እንደሚቻልም አስረድተዋል፡፡

ዳያስፖራው ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው መሠረታዊ አጀንዳዎችን ነቅሶ በማውጣት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

ዳያስፖራው ግልጽ እንዲሆንለት የሚፈልገውን ጉዳይ ለመጠየቅ እና ኢትዮጵያን የሚጠቅም አጀንዳ ለማስያዝ ዝግጅት እንዲያደርግም ነው ፕሮፌሰር መስፍን ጥሪ ያቀረቡት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም