ከ65 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሐድሶ ሂደት አልፈው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል - ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
ከ65 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሐድሶ ሂደት አልፈው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል - ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2017(ኢዜአ)፦ የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን 65ሺህ 500 የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሃድሶ ሂደት በማሳለፍ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረጉን ገለጸ።
የፌዴራል መንግሥት የቀድሞ ታጣቂዎችን ለማሰልጠን፤ ለስልጠና ማዕከላት ጥገና፣ ለምግብ፣ ለአልባሳት እንዲሁም ለተለያዩ ጉዳዮች እስከአሁን አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ማውጣቱ ተጠቁሟል።
የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸውን ጉዳዮች በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ኮሚሽኑ 65ሺህ 500 የቀድሞ ታጣቂዎች በተሐድሶ ሂደት አልፈው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረጉን ገልጸዋል።
እነዚህ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመጡት ትጥቅ የማስረከብ፣ የማረጋገጥ፣ ምዝገባ የማካሄድ፣ የተሀድሶና የስነ ልቦና ሥልጠና በመውሰድ እንዲሁም የዲጂታል መታወቂያ አግኝተው ወደ ህብረተሰቡ የተቀላቀሉ መሆናቸውም ተጠቁሟል።
የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን እንደተናገሩት፤ ኮሚሽኑ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊና ምርታማ ህይወት ለማሸጋገር በርካታ ስራዎችን አከናውኗል።
ኮሚሽኑ በሰላም ስምምነት እንዲሁም በመንግስት፣ በሀገር ሽማግሌዎችና በሀይማኖት አባቶች የቀረቡ ጥሪዎችን ተቀብለው ወደ ሰላም የሚመጡ የቀድሞ ታጣቂዎች የሀገሪቱ የሰላምና የልማት ኃይል እንዲሆኑ ለማስቻል እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከህዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ወዲህ ከ65ሺህ 500 የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሃድሶ ሂደት በማሳለፍ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን ጠቁመዋል።
ይህም በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች መሆኑንም አስታውቀዋል።
የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ተስፋለም ይህደጎ በተለያዩ ክልሎች የተሐድሶ ማዕከላትን በማቋቋም የቀድሞ ታጣቂዎችን በዘላቂነት እንዲቋቋሙ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በትግራይ ክልል በሶስት ማዕከላት የቀድሞ ታጣቂዎችን ተቀብሎ በተሐድሶ ሂደት በማሳለፍ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
የፌዴራል መንግሥት ለስልጠና ማዕከላት ጥገና፣ ለምግብ፣ ለአልባሳት እንዲሁም ለተለያዩ ጉዳዮች አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ማውጣቱን ጠቁመው፤ የቀድሞ ታጣቂዎቹን ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ ለእያንዳንዳቸው 90ሺህ 400 ብር መሰጠቱን እና በአጠቃላይ ከአጋር አካላት አምስት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
በየትኛውም አካባቢ ያሉ ታጣቂዎች የሕዝብንና የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው የተሐድሶ መርሐ ግብሩ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።
የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ በመግለጫቸው፤ ኮሚሽኑ ወደ ስራ ከገባ ወዲህ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲቀላቀሉ መደረጉን ተናግረዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ስራ ከፍተኛ ሀብት የሚፈልግና ፈታኝ ተግባር መሆኑንና የመንግስት፣ የህዝብንና የአጋር አካላትን ትብብር እንደሚጠይቅ አመልክተው፤ ይህ የሚመራበት የመልሶ ማቋቋሚያ ሰነድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ሰነዱ በሚመለከታቸው አካላት የተተቸና በቅርቡ እንደሚጸድቅ ጠቁመው፤ በሰነዱ መሰረት የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ወደ ማቋቋም ተግባር እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዚህም በተሐድሶ ሂደት አልፈው የኮሚሽኑን ህጋዊ መታወቂያ የያዙ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ቀደመ ስራቸው እንደሚመለሱና ጥቅማ ጥቅሞች እንደሚከበርላቸውም ጨምረው አስታውቀዋል።
በተሃድሶ ሂደት አልፈው ከህብረተሰቡ ጋር ለተቀላቀሉ የቀድሞ ታጣቂዎች አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።