ቀጥታ፡

የትውልድ የስብእና ግንባታ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ከፍተኛ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2017(ኢዜአ)፦ ትውልድን በስብእና መገንባት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ከፍተኛ ሚና እንዳለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

4ኛው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ዘርፎች የጋራ ጉባኤ በቢሾፍቱ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።


 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቅሰሙ ማሞ በዚህ ወቅት፤ የሴቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶችና አረጋውያን ጉዳይ የአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

በዚህም የተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር በማጎልበት ኢትዮጵያን የሚያሻግር ትውልድ መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የትውልዱ የስብእና ግንባታ የተሻለች ኢትዮጵያን የመገንባት አጀንዳ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በስብእና የተገነባ ትውልድ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የማሸጋገር አቅሙ ከፍተኛ ነው ያሉት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ፤ የአዲስ አበባን የቅድመ ልጅነት መርኃ ግብር ምርጥ ተሞክሮ ሌሎች ከተሞች በመቅሰም ሊተገብሩት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም የሴቶች፣ ህፃናት፣ አረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች ሁኔታ ላይ የክትትልና ድጋፍ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች የማህበራዊ ጥበቃ ሥርዓትን በማጠናከር የሴቶች፣ ህፃናት፣ አረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች መብት እንዲጠበቅ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የክትትልና የድጋፍ ስርዓቱን ለማጠናከር የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ።

በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ሳቢያ ማህበራዊ ድጋፍ የሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ የሁሉም አካላት ርብርብ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የማህበራዊ ጥበቃ ተደራሽነትን ለማስፋት ቅንጅታዊ አሰራሮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር ምክትል የቦርድ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ክፍሌ፤ የአዲስ አበባ ከተማ የአረጋውያን አካቶ ትግበራ በዕድሜ የገፉ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አባይነህ ጉጆ፤ ባለፉት ዓመታት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ስኬታማ የማዕከላት ግንባታና የፖሊሲ እርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ፉአድ ገና፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ የወጣቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም