ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፋችንን እናጠናክራለን - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፋችንን እናጠናክራለን
ነቀምቴ ፤ ነሐሴ 6/2017 (ኢዜአ)፡-ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ በነቀምቴ ከተማ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋንጫ ነቀምቴ ከተማ ሲደርስ የተገኙ የአራቱ የወለጋ ዞኖች እና የነቀምቴ ከተማ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል።
በአቀባበሉ ከተሳተፉት መካከል ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የመጡት ኮማንደር ጋሩማ ሱታ ፤ ሕዳሴ ግድብ መገንባቱ የውሃ ሀብትን በፍትሀዊነት በመጠቀም በራስ አቅም መልማት እንደምንችል ያረጋገጠ ታላቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ለዚህ ታላቅ ፕሮጀክት ስራ ከተመጀረበት ጊዜ አንስቶ ያደረጉትን ድጋፍ በቀጣይም እንደሚያጠናክሩ አስታውቀዋል።
የነቀምቴ ከተማ ነዋሪው ኮማንደር ሙሉ ገመቹ በበኩላቸው፤ ለግድቡ ግንባታ የበኩላቸውን በማዋጣት አሻራቸውን ማኖራቸውን ተናግረዋል።
ሌላኛው የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ ተስፋዬ አጋ ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገራችንን የመልማት ህልም ያሳካ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ለግንባታው የበኩላቸውን ከማዋጣት ባለፈ ሌሎችን በማስተባበር ጭምር ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ምስጋኑ ቱሉ ፤ የለውጡ መንግስት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ተጀምረው የዘገዩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ከፍፃሜ በማድረስ አኩሪ ተግባር ማከናወኑን ተናግረዋል።
ሕዝቡ ይህን ታሪካዊ ግድብ እውን እንዲሆን በሚደረገው ርብርብ ቀደም ሲል ካበረከተው አስተዋጽኦ ባለፈ ዛሬ ላይ ዋንጫውን በመቀበል ተጭማሪ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን እንዳረጋገጠ ገልጸዋል።
የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዋቅጋሪ ነገራ ፤ የአራቱም የወለጋ ዞኖች የአስተዳደር አካላት፣ የፖሊስ አባላት ፣የሴክተር ሀላፊዎችና ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች "ዛሬ አብረን የጀመርነውን አብረን እንጨርሳለን እንኳን በሰላም መጣችሁ" ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴው ግድብ የሕብረተሰቡ የገንዘብ ፣የጉልበትና የእውቀት ጣምራ ውጤት መሆኑንም አንስተዋል።
ተግባሩንም ለማስቀጠል ሁለንተናዊ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።