ቀጥታ፡

መንግስት ለቅርስ ዕድሳት የሰጠው ትኩረት የቅርሶችን ደኅንነት መጠበቅ አስችሏል - ባለስልጣኑ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት ለቅርስ ዕድሳት የሰጠው ትኩረት የቅርሶችን ደኅንነት መጠበቅ እንዳስቻለ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ገለጸ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ለኢዜአ እንዳሉት፤ መንግስት ለቅርስ እንክብካቤ የሰጠው ትኩረት የቅርሶችን ደኅንነት ለመጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

በተለይም ከለውጡ ወዲህ መንግስት ቅርስ ሀብት ነው መልማት አለበት በሚል በቅርስ ጥበቃ ላይ የፈጠረው አዲስ ዕይታ ኢትዮጵያ ያላትን የካበተ የቅርስ ሃብት በመጠበቅ ወደ ሃብት መቀየር እያስቻለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም በርካታ የኢትዮጵያ የቅርስ ሃብቶች ላይ የዕድሳትና እንክብካቤ እንዲሁም የጥገና እና የልማት ስራ እንዲከናወን ማስቻሉን ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ የተከናወኑና በመከናወን ላይ የሚገኙ የቅርስ ዕድሳትና እንክብካቤ ስራዎችም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር በተሞክሮነት የሚቀርቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያውያንን ገናና ታሪክ በማስተዋወቅና ትውልድን በማነጽ ትልቅ ድርሻ ያለው የቅርስ ሃብትም በሀገር የቱሪዝም ገቢ ላይ ጉልህ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት የተከናወኑና እየተከናወኑ የሚገኙ የቅርስ ዕድሳት እና ልማት ስራዎች የኢትዮጵያን ቅርሶች ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲሁም ልማት የሰጡት ትኩረት ለቅርሶች ደኅንነትና ልማት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ነው ጨምረው የተናገሩት።

ብሔራዊ ቤተ-መንግስት፣ አንድነት ፓርክ፣ የጎንደር አብያተ-መንግስታት እና የጅማ አባ ጅፋር ቤተ-መንግስት የቅርሶችን ታሪካዊነትና የሀገርን ከፍታ በሚመጥን መልኩ የታደሱበትን መልካም አጋጣሚ መፍጠሩንም አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን በአሁኑ ወቅት የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናትን፣ የአክሱም ሐውልቶችን፣ የብሔራዊና የደሴ ሙዚየሞችን ጨምሮ ሌሎች ቅርሶችን የመጠበቅ፣ የመንከባከብና የማደስ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እድሳት የሚደረግላቸው የቅርስ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ ውስጥ በተሻለ ጥራት እንዲጠናቀቁ ትኩረት መደረጉንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም