ቀጥታ፡

ጉባኤው አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ የታዳሽ ኃይል ልማትና ሌሎች የተግባር መፍትሔዎቿን የምታሳይበት ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2017(ኢዜአ)፦ ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ጉባኤ አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ የታዳሽ ኃይል ልማትና ሌሎች የተግባር መፍትሔዎቿን የምታሳይበት መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ(ዶ/ር) ተናገሩ።

ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አስመልክቶ የቅድመ ጉባኤ ኤግዚቢሽን በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ግቢ ተከፍቷል።

ኤግዚቢሽኑ የኢነርጂ ሽግግር ጉዞ ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለአፍሪካ የማይበገር እና ዝቅተኛ የካርቦን ልቀትን መሰረት ያደረገ ታዳሽ ኃይል ለመገንባት በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ የጋራ ሥራዎችን ለማሳየት ያለመ ነው።


 

በኤግዚቢሽኑ የተለያዩ የመንግስት እና የግል ተቋማት በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ እየሰሩ ያሉትን ስራ ይዘው ቀርበዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመከላከልና ለመቀነስ የተለያዩ ኢንሼቲቮችን እየተገበረች ትገኛለች።

ለአብነትም የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ በመንደፍ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እያከናወነች ያለችውን ሥኬታማ ስራ አንስተዋል።

ይህም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅእኖ ለመከላከልና ለመቀነስ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

እንዲሁም የታዳሽ ኃይል ልማትን በማስፋት ተፅእኖን ለመከላከልና ለመቀነስ ትኩረት መስጠቷን ጠቁመው፥ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አፍሪካውያን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በተመለከተ ድምጻቸውን በጋራ የሚያሰሙበት ነው ብለዋል።

አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከልና ለመቀነስ በራሷ አቅም እያከናወነቻቸው ያሉ የታዳሽ ኃይል እና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ለዓለም የሚታሳይበት መድረክ እንደሆነም ተናግረዋል።

በተቋሙ የተከፈተው ኤግዚቢሽን ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ጠንካራ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እየገነባች መሆኗን የሚያስቃኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

ከኤግዚቢሽኑ ተሳታፊዎች መካከል የአራራት ኢነርጂ ማናጀር ናሆም ኃይሉ፥ ኤግዝቢሽኑ እንደ ሀገር በታዳሽ ኃይል ልማት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ለማስተዋወቅ ያስችላል ብለዋል።


 

የመሰረት ማሬ የሶላር ምርቶች ባለሙያ የሆነው ይድነቃቸው ድርሻዬ በበኩሉ የታዳሽ ኃይል ልማት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ጉልህ ፋይዳ እንዳለውና በትኩረት እየሰሩበት መሆኑን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም