ቀጥታ፡

የብልጽግና ፓርቲ ያከናወናቸው ሁሉን አቀፍ ስራዎች ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው-አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 6/2017 (ኢዜአ)፡-የብልጽግና ፓርቲ ያከናወናቸው ሁሉን አቀፍ ስራዎች ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

12ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ “ከፖለቲካ ወደ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በጋና አክራ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል፡፡


 

በመድረኩ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ እና የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) እየተሳተፉ ነው።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በዚህ ወቅት፥ ፖለቲካ በአፍሪካ ለረጅም ዓመታት የኃይል ሽኩቻ፣ የአጭር ጊዜ አጀንዳዎች ማስፈጸሚያ እና የተቀናቃኝነት አውድማ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።

ከዜሮ ድምር እሳቤ በመውጣት ፖለቲካ የሀገራት ሁሉን አቃፊነት፣የብልጽግና እና የሰላም መሳሪያ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ከጠባብ የፖለቲካ እሳቤ ወደ አካታችነት መሸጋገር የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሪፎርም አብይ አስኳል እንደሆነ ተናግረዋል።

ብልጽግና የተለያዩ ፓርቲዎች ተዋህደው ያቋቋሙት ፓርቲ መሆኑን ገልጸው፥ በዚህም በብዝሃ እሳቤ ሀገራዊ ራዕይን ለማሳካት የሚሰራ ፓርቲ ነው ብለዋል።

ፓርቲው ራዕዩን በመደመር እሳቤ በመቃኘት መዳረሻውን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር እሳቤ በብዝሃ ማንነት ውስጥ ያሉ አቅሞችን በጋራ በመጠቀም ብልጽግናን እውን ማድረግን ያለመ መሆኑን አመልክተዋል።


 

ብልጽግና ፓርቲ የመደመር እሳቤ ከንግግር በማሻገር ለብሄራዊ ጥቅም እና ለዴሞክራሲ ስርዓት መረጋገጥ ሲባል በምርጫ ባሸነፈበት መንግስት ውስጥ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች እንዲካተቱ ማድረጉን ተናግረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መሳተፍ አሳታፊነትን ለማረጋገጥ፣ብሄራዊ መግባባት እና አንድነትን ለመገንባት እንዲሁም መረጋጋት እና ዘላቂ ልማትን ለማምጣት ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሁሉንም ህጋዊ ፓርቲዎች በማካተት ለውይይት፣ምክክር እና መግባባት መገንቢያ ቋሚ ማዕቀፍ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የሴቶች እና ወጣቶችን ተሳትፎ የሚያሳድጉ ተጨባጭ ስራዎችን ማከናወኑን አመልክተዋል።

በመንግስት ካቢኔ ውስጥ 50 በመቶ ሴቶች እና በሁሉም ደረጃ ከሚገኘው የአስተዳደር እርከን ውስጥ 49 በመቶው በወጣት እየተመራ መሆኑን በዋና ማሳያነት አቅርበዋል።

ሀገር በቀል ሪፎርም ዘላቂ ልማት እና ፍጹም ሉዓላዊነት ማረጋገጥን ታሳቢ በማድረግ እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልጸው፥ከተረጂነት ወደ ምርታማነት መርህ ሚሊዮኖችን ከተረጂነት በማውጣት የዜጎችን የምርታማነት አቅም የማሳደግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

በብዝሃ ማህበረሰብ ውስጥ መግባባት ወሳኝ ነው ያሉት አቶ አደም፥ በዚህ ረገድም መንግስት ሁሉን አሳታፊ በሆነው የሀገራዊ ምክክር ታሪካዊ ክፍፍሎች መቋጫ እንዲያገኙ፥ አግኝተው ሀገራዊ ተግባቦት እንዲፈጠር አበክሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የትምህርት እና ጤና አቅርቦትን በማስፋት፣የኮሪደር ልማትን እና የተለያዩ የልማት ፕሮግራሞችን በመተግበር እንዲሁም የማህበረሰብ ዋስትና ጥበቃ ስራን ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ በማከናወን የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ አማካኝነት እስከ አሁን ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና ልማትን ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ያከናወናቸው ስራዎች ለአፍሪካ ሀገራት ትምህርት የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።

የፖለቲካ ስኬቶችን ምርጫ በማሸነፍ ብቻ መመዘን እንደማይገባና በዜጎች ህይወት ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ቁልፍ መለኪያ መሆን አለበት ነው ያሉት።

የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ቀጣይነት ያለው የገዢ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ውይይት ማድረግ፣ ወጣቶች ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ አጀንዳዎች መተግበር እና አረንጓዴና ዲጂታል ሽግግር ላይ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና አካታችነትን ማረጋገጥ ከተቻለ ከፖለቲካ ወደ ብልጽግና የሚለውን እሳቤ በተጨባጭ እውን ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል።

12ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ እስከ ነሐሴ 8 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

ጉባኤው በቀጣናዊ ትስስር፣ሰላምና ፀጥታ፣ሁሉን አቀፍ አሥተዳደር፣ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና በአህጉራዊ ልማት በሚሉ አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም