ቀጥታ፡

በባሌ ዞን የቡና ምርታማነት ተሻሽሏል

ባሌ ሮቤ፤ ሐምሌ 6/2017 (ኢዜአ)፡- በባሌ ዞን ከአምራቹ አርሶ አደር ጀምሮ በየደረጃው በተከናወነው ስራ የቡና ምርታማነት ማሻሻል መቻሉን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

የቡና ምርት፣ ጥራትና ግብይት ማሻሻልን ዓላማ ያደረገ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በባሌ ሮቤ ከተማ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር ፕሬዚዳንት በተገኙበት በተካሄደው በዚሁ መድረክ ላይ የባሌ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ጌታቸው አበበ እንደተናገሩት፤ በዞኑ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

ይህም ከአርሶ አደሩ ጀምሮ በየደረጃው በተከናወነው ስራ የቡና ምርታማነት መሻሻሉን ገልጸዋል።

የቡና ምርታማነትን በአማካይ ከስድስት ወደ ስምንት ኩንታል ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም የዞኑን የቡና ሽፋን ባለፈው ዓመት ከነበረበት 53ሺህ ሄክታር ወደ 68ሺህ ሄክታር ማድረስ መቻሉን አክሏል።

የቡና አምራቾች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎችን በአንድ ላይ ያገነኛው የውይይት መድረክ በቡና ምርትና ግብይት ዘርፍ የሚታዩ ተግዳሮችን ለመፍታት እገዛ እንዳለውም አንስተዋል።

እንዲሁም በዞኑ በበጀት ዓመቱ ለመዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የታቀደውን 15ሺህ ቶን ቡና ለማሳከት መደላድል እንደሚፈጥርም እንዲሁ።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር ፕሬዚዳንት ሁሴን አምቦ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ማህበሩ በሀገር ደረጃ የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን በመደገፍ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በአምራቹ አርሶ አደር፣ በአቅራቢዎችና ላኪዎች ዘንድ የሚስተዋለውን የግንዛቤ ክፍተት በመሙላት የቡና ምርታማነትና ግብይት ላይ ለውጥ መጥቷል ብለዋል።

በቡና ጥራት ችግርና በግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ የሚታዩ ህገ-ወጥ ሥራዎች ትኩረት የሚሹ የማህበሩ ቀጣይ የቤት ሥራ እንደሆነም አንስተዋል።

በባሌ ሮቤ በቡና ምርትና የግብይት ሰንሰለት ውስጥ ተዋናይ ከሆኑ አካላት ጋር የተካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ የዚሁ ጥረት አካልና ቀጣይነት ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች፤ ምክክሩ በቡና ምርትና የግብይት ሰንሰለት ውስጥ ሲያጋጥማቻው የቆዩ ተግዳሮቶች ተለይተው

እልባት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም