ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የወደፊት ዲፕሎማሲ የሚመሩ ወጣቶችን ለማፍራት ወደ ተግባር ተገብቷል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2017(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያን የወደፊት ዲፕሎማሲ የሚመሩ ወጣቶችን ለማፍራት ወደ ተግባር መገባቱን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የተማሪዎች የክረምት በጎ ፈቃድ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ስልጠና ዛሬ አስጀምሯል፡፡


 

በክረምት በጎ ፈቃድ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ስልጠናው ጥብቅ በሆነ መስፈርት ተመዝነው ያለፉ ተማሪዎች የሚሳተፉበት መሆኑም ተገልጿል፡፡ 

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢንስቲትዩቱ በውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዙሪያ ምርምርና ስልጠና ይሰጣል፡፡

የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፋንታ በወጣቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የምትከተለው የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የወጣቶችን ንቁ ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የወጣቱ ትውልድ ድምጽ ችላ የሚባልበት ዘመን አልፏል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የክረምት በጎ ፈቃድ የዲፕሎማሲ ስልጠና የወጣቶች ተሳትፎ ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወጣቶች በስልጠናው የድርድር፣ የተግባቦት እና የንግግር ክህሎታችውን በማሳደግና የፈጠራ አቅማቸውን በመጨመር መሰረታዊ ዕውቀት ይጨብጣሉ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለማሳካት የተለመችውን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለማሳካት ከመደበኛው ዲፕሎማሲ ባሻገር የወጣቶችን ንቁ ተሳትፎ እንደሚጠይቅም ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው የኢትዮጵያን የወደፊት ዲፕሎማሲ የሚመሩና የሚቀርጹ ወጣቶችን ለማፍራት እንደሚያግዝ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲፕሎማቶች የተሰጥኦ ማዕከል መፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡

ወጣቶች በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ እድገትና ዓለም አቀፍ ተሳትፎ የጎላ አበርክቶ እንዲኖራቸው ያስችላልም ብለዋል፡፡


 

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የባለድርሻ አካላት ዘርፍ ዳይሬክተር ጄኔራል መላኩ ሙሉዓለም የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ የተቋማት ብቻ አይደለም ብለዋል፡፡

በዲፕሎማሲ ውስጥ ሌሎችም አጋዥ አካላት እንደሚያስፈልጉ በመግለጽ፤ ፓርላሜንታሪ ዲፕሎማሲ ሚሊታሪ አታሼ የዲፕሎማሲ አቅምን እንደሚያጎለብቱ ገልጸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ በሚያስችሉ ዲፕሎማሲያዊ፣ ዓለም አቀፍ ህጎች እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ምርምር ያደርጋል ብለዋል፡፡


 

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ተመራማሪና አሰልጣኝ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሁሉም ዜጎች የሀገራቸው ዲፕሎማቶች ናቸው ብለዋል፡፡

ወጣቶች በዲፕሎማሲ ቋንቋ እንዲጽፉና የሀገራቸውን ነባራዊ ሁኔታ ለዓለም ማስረዳት እንዲችሉ በውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዙሪያ መሰረታዊ እውቀትና ክህሎት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም