በአፋር ክልል በመካከለኛውና ታችኛው አዋሽ የውሃ ሙላት የስጋት ቀጣናዎች የቅድመ ጥንቃቄ ስራ ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል በመካከለኛውና ታችኛው አዋሽ የውሃ ሙላት የስጋት ቀጣናዎች የቅድመ ጥንቃቄ ስራ ተከናውኗል

ሠመራ፣ ነሐሴ 6/2017(ኢዜአ) ፡-በአፋር ክልል በመካከለኛውና ታችኛው አዋሽ የውሃ ሙላት የስጋት ቀጣናዎች የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
በአዋሽ ተፋሰስና በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍና የወንዝ ውሃ ሙላት የመከሰት ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል።
ይኸንኑ ስጋት ከግምት በማስገባት የአዋሽ ወንዘ ተፋሰሶችን የጎርፍ አደጋ ስጋት ለመከላከል የሚያስችል ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጣ ልዩ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል።
ግብረ ሃይሉም በአካባቢው የጎርፍ አደጋ ቢከሰት አስቀድሞ ጥንቃቄ ለማድረግ፣ አስፈላጊውን ምላሽ ለመስጠትና የመልሶ ማቋቋም ስራ ለማከናወን የሚያስችል ነው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ለኢዜአ ማብራሪያ የሰጡት የአፋር ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር መሐመድ ሁሴን፤ በመካከለኛውና ታችኛው አዋሽ የጎርፍ አደጋ ስጋት ያለባቸው ቀጣናዎች ተለይተው የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የአዋሽ ወንዝ ከዚህ ቀደም ያደርስ የነበረውን ጉዳት ከግንዛቤ በማስገባት አደጋው ከመከሰቱ በፊት የጥንቃቄ ሥራ፤ ቢከሰትም መከላከል የሚያስችል ዝግጁነት ስለመኖሩ አረጋግጠዋል።
ይህንንም ለማከናወን በስፍራዎቹ ሁለት ጀልባዎች ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰው የምግብ፣ የውሃ፣ የመጠለያና የመድሃኒት እንዲሁም በቤት ቁሳቁሶች ከመንግስትና ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
በዚህ ወቅት ለሚነሱ አደጋዎች የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የክልሉ መንግስት የመጠባበቂያ በጀት የያዘ መሆኑን ጠቅሰው አቅምን ባማከለ መልኩ አስፈላጊ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩት የማህበረሰብ ክፍሎችም ባገኙት የጥንቃቄ መረጃዎች ከአካባቢው አስተዳደሮች ጋር በመተባበር የጥንቃቄ ሥራ መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የሐይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎችና በየደረጃው ያሉ የአመራር አካላትም በእነዚህ የስራ ክንውኖች ወቅት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
በአፋር ክልል ለጎርፍ አደጋ የስጋት አካባቢ ተብለው በ13 ወረዳዎች ውስጥ 62 ቀበሌዎች የተለዩ መሆኑም ታውቋል።