ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በጋራ ማሳካታችን በሌሎች የልማት ስራዎች ያለንን ተነሳሽነት የሚያጎላ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተባበረ ጥረት ማሳካታችን በሌሎች የልማት ስራዎች ያለንን ተነሳሽነት የሚያጎላ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ዙሪያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቁንና በቅርቡም በጋራ ሪቫን በመቁረጥ ለኢትዮጵያ ህዝብ እናበስራለን ማለታቸው ይታወቃል።

ግድቡ በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት እውን የሆነ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፤ የግድቡን መሳካት በተመለከተም ኢዜአ በአዲስ አበባ ተዘዋውሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አነጋግሯል።

ከመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል ሞገስ አያሌው ለግድቡ ግንባታ ቦንድ ከመግዛት፣ ስለ ግድቡ ያላቸውን ግንዛቤ ለሌሎች በማካፈል የበኩላቸውን ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።


 

የህዳሴ ግድቡ በቅርቡ የሚመረቅ መሆኑ እንዳስደሰታቸው በመግለጽ ግድቡ የተሳካው ኢትዮጵያውያን ለጋራ ሀገራዊ ልማት በአንድነት በመቆማችን ነው ብለዋል።

ወጣት ሰላም በላይነህ በበኩሏ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እኛ ወጣቶች ሁሌም በኩራት የምናነሳው ትልቅ ሀብታችን ነው ብላለች።


 

ቀደምት አያቶቻችን በዓድዋ ድል ሀገርን ከነክብሯ ለትውልዱ ማስረከባቸውን ገልጻ፥ እኛም ከአባቶቻችን በወረስነው ጀግንነት  ግድቡን በላባችን በማሳካት አዲስ የድል ታሪክ ጽፈናል ነው ያለችው።

ህዳሴ ግድብ በቅርቡ የሚመረቅ መሆኑ  ለህዝቡ ትልቅ የድል ዜና ነው ያሉት ደግሞ እዮስያስ ዮሴፍ ናቸው።


 

የግንባታው መጠናቀቅ ለሀገር ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውና ለቱሪዝም መስህብነት ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ ይህ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የእውቀት እና የክህሎት ሽግግር እንዲያደርጉ ምች ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ ወጣት ብሩክ አማኑኤል ትልቅ የሀገር ሀብትና እውቀት የፈሰሰበትን የሕዳሴ ግድብ ሊመረቅ መሆኑ አስደስቶኛል ብሏል፡፡


 

የመዲናዋ ነዋሪዎች አክለውም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራስ አቅም ሌሎችንም ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚቻል ያስተማረና መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

 በልማት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ለሀገር ዕድገት ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም