ቀጥታ፡

ራዕያችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነች እና ለትውልዱ አሻራዋንና የዕድገት ትሩፋቷን የምታወርስ ኢትዮጵያን መገንባት ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2017(ኢዜአ)፦ራዕያችን  የላቀ የግንባታ አቅም የፈጠረች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነች እና ለትውልዱ አሻራዋንና የዕድገት ትሩፋቷን የምታወርስ ኢትዮጵያን መገንባት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ  ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንፎርሜሽን ኢኒሼቲቭን በይፋ አስጀምረዋል።


 

ኢኒሼቲቩ እ.አ.አ ከ2025  እስከ 2050 ዓም የሚተገበር ሲሆን ዘርፉን ተወዳዳሪ በማድረግ ውጤታማ ስራዎችን በተቀናጀ መንገድ  ገቢራዊ ማድረግ የሚያስችል ነው ተብሏል።

በኢኒሼቲቩ ይፋ በማድረጊያ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፥ መንግሥት ተግባራዊ ባደረጋቸው የለውጥ እርምጃዎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በማጠናቀቅ ረገድ ውጤታማ እንዲሆን  ማስቻላቸውን ተናግረዋል።

የመንግስታችን ባህሪ አርቆ ማየት፣ በሰፊው ማቀድ እና ምልዓተ ህዝቡን አሳትፎ አልቆ በፍጥነት መፈፀም ነው  ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በዚህም ለረዥም ዓመታት ቃል የተገቡ፣ የተጓተቱ እና በውስብስብ ችግር ቆመው የነበሩ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ በማስገባት ማጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን በጥራት መፈጸምን መገለጫችን አድርገነዋል ነው ያሉት።

ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች  አበረታች ቢሆኑም አሁንም ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ገልጸው፥ በቀጣይ ተከታታይ ኢንሼቲቮችና ሜጋ ፕሮጀክቶች  ተጠናክረው  እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በመሆኑም የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተዋንያን በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን በመከተል ለግንባታ ጥራትና ፍጥነት እንዲሁም ለስራ ዕድል ፈጠራ በላቀ ቁርጠኝነት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ትልቅ አቅም ያለው ዘርፍ መሆኑን ጠቁመው ከዘርፉ በሚጠበቀው ደረጃ ተጠቃሚ ለመሆን ቅንጅታዊ አሰራር ሊጠናከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዚህ ረገድ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ኢንዱስትሪው ያለበትን አጠቃላይ ሁኔታ በመዳሰስ፤ ከዚህ በፊት የነበሩትን አካሄዶች በመፈተሽ ትርጉም ባለው መንገድ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪን ትራንስፎርሜሽን ኢንሼቲቭን ይፋ ማድረጉን አድንቀዋል።

እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ኢኒሼቲቩ የዘርፉን አጠቃላይ ተግዳሮቶች የለየ፣ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ፣ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ከሀገር አልፈው በአፍሪካ ጭምር ዐሻራቸውን ማሳረፍ እንዲችሉ በማድረግ ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።

ስራን መሰረት ያደረገ የዘርፉ ተዋናዮች ምዘና፣ ደረጃ እና እውቅና አሰጣጥና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን መሆኑን ገልጸው፥ ይህም ዘርፉን ውጤታማ፣ ለውጥ የሚታይበት፣ በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችል አመላካች ነው ብለዋል፡፡


 

መንግስት ከአሁኑ በበለጠ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን የሚያሳትፉ ሰፋፊ ሥራዎችን፣ ፕሮግራሞችን፣ ሜጋ ፕሮጀክቶችን  በማቀድ በተከታታይም ይፋ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ ራዕያችን የላቀ የግንባታ አቅም የፈጠረች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነች እና ለትውልዱ አሻራዋንና የዕድገት ትሩፋቷን የምታወርስ ኢትዮጵያን መገንባት ነው ብለዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እያደረገ ያለውን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ በማጠናከር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ሀገርን የሚያኮራ እንዲሆን አበክሮ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ኢኒሼቲቩ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጣ ባለሙያዎችን በማብቃት፣  ኩባንያዎችንና ድርጅቶችን በማዘመን፣ ዘርፉን  በአሳታፊ ዘመናዊና ወጥ አሰራር መምራት እንደሚያስፈልግም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፅንኦት የሰጡት።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፤ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ  ዘርፉን በማዘመን ሀገራዊ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ መሆኑን  ገልጸዋል።


 

የኮንስትራክሽን ዘርፉ ዕድገት በተለያዩ ምክንያቶች በሚጠበቀው ደረጃ ላይ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ የኢኒሼቲቩ እውን መሆን ትልቅ ፋይዳ  እንዳለው ተናግረዋል።

 በመስኩ የሰው ኃይል ልማት ማሳለጥ እንዲሁም የስራ ዕድል ፈጠራን  በተቀናጀ  አግባብ  ማስኬድ  ከኢኒሼቲቩ  ግቦች መካከል  መሆኑን አብራርተዋል።

አማካሪዎች እና ተቋራጮችን በመመዝገብ ደረጃ እንዲሰጣቸው የሚደረግ መሆኑን ጠቁመው ተቋራጮችና አማካሪዎች ከኢትዮጵያ አልፎ በጎረቤት ሀገራት መስራት እንዲችሉ አስፈላጊው  ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ኢኒሼቲቩ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑንም  ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም