ቀጥታ፡

የኮንስትራክሽን ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ ሀገራዊ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ ነው -ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2017(ኢዜአ)፦ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ ዘርፉን በማዘመን ሀገራዊ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

እ.አ.አ ከ2025 እስከ 2050 የሚተገበር ሀገር አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ ዛሬ ይፋ ተደርጓል።

ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በዚህ ወቅት፥ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ዕድገት በተለያዩ ምክንያቶች በሚጠበቀው ደረጃ ላይ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።

በዚህ ረገድ የኢኒሼቲቩ እውን መሆን ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።


 

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከውጭ በሚገባው ግብዓት ላይ የተመረኮዘ መሆኑ ከፈተናዎቹ መካከል እንደሆነ ጠቅሰው፥ ለዚህ ዘላቂ እልባት ማበጀት የኢኒሼቲቩ ሌላው ዓላማ ነው ብለዋል።

በመስኩ የሰው ኃይል ልማት ማሳለጥ እንዲሁም የስራ ዕድል ፈጠራን በተቀናጀ አግባብ ማስኬድ ከኢኒሼቲቩ ግቦች መካከል መሆኑን አብራርተዋል።

አማካሪዎች እና ተቋራጮችን በመመዝገብ ደረጃ እንዲሰጣቸው የሚደረግ መሆኑን ጠቁመው፤ ተቋራጮችና አማካሪዎች ከኢትዮጵያ አልፎ በጎረቤት ሀገራት መስራት እንዲችሉ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ኢኒሼቲቩ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም