ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል የታዳሽ ኃይል ልማትን እያስፋፋች ነው - የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል የታዳሽ ኃይል ልማትን እያስፋፋች ነው - የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል የታዳሽ ኃይል ልማትን እያስፋፋች እንደምትገኝ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) ገለጹ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አስመልክቶ ቅድመ ጉባኤ ኤግዚቢሽን እያካሄደ ይገኛል።
ኤግዚቢሽኑ የኢነርጂ ሽግግር ጉዞ ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለአፍሪካ የማይበገር እና ዝቅተኛ የካርቦን ልቀትን መሰረት ያደረገ ታዳሽ ኃይል ለመገንባት በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ የጋራ ሥራዎችን ለማሳየት ያለመ ነው ተብሏል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በኤግዚቢሽን መክፈቻው ላይ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመከላከል እና ለመቀነስ የተለያዩ ኢንሼቲቮችን በመንደፍ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች።
ለአብነትም የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ በመንደፍ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እያከናወነች ያለችውን ሥኬታማ ስራ አንስተዋል።
ይህም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመከላከል እና ለመቀነስ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
እንዲሁም የታዳሽ ኃይል ልማትን በማስፋት ተፅዕኖን ለመከላከል እና ለመቀነስ ትኩረት መስጠቷን ገልጸው፥ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።