የግብር አከፋፈል ስርአቱ የዲጂታል አሰራርን የተከተለ በመሆኑ በቀላሉ ለመክፈል አስችሎናል- ግብር ከፋዮች - ኢዜአ አማርኛ
የግብር አከፋፈል ስርአቱ የዲጂታል አሰራርን የተከተለ በመሆኑ በቀላሉ ለመክፈል አስችሎናል- ግብር ከፋዮች
አዳማ፤ ነሐሴ 6/2017(ኢዜአ)፦ የግብር አከፋፈል ስርአቱ የዲጂታል አሰራርን የተከተለ በመሆኑ በቀላሉ ለመክፈል አስችሎናል ሲሉ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ገለጹ።
የዞኑ ገቢዎች ጽህፈት ቤት በበኩሉ ከደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ከ154 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል።
በኦለንጪቲ ከተማ በካፌና በሱፐርማርኬት ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ አስማማው ዳኜ፤ የንግድ እንቅስቃሴያቸውን በካሽ ሪጅስተር ማድረጋቸው ገቢያቸውን በማሳወቅ ግብራቸውን በወቅቱ መክፈላቸውን ተናግረዋል።
የግብር አከፋፈል ስርአቱ ዘመናዊና በዲጂታል ሲስተም የተደገፈ በመሆኑ በቀላሉ መስተናገድ ስለመቻላቸውም አንስተዋል።
የዲጂታል አሰራሩ የግብር ተመን ለማወቅ ወደ ማእከል በመሄድና ባንክ ቤት ወረፋ በመጠበቅ የሚያጠፉትን ጊዜና ገንዘብ ያስቀረ መሆኑን ገልጸው ለተፈጠረው ምቹ ሁኔታ አመስግነዋል።
በዞኑ ሉሜ ወረዳ በቁም እንስሳት ንግድ የተሰማሩት አቶ ሄኖክ ታደሰ፤ የሀገር ልማት የሚሰራውና እድገትም የሚመጣው በግብር በመሆኑ ብዙዎቻችን በዚሁ ልክ ግዴታችንን እየተወጣን እንገኛለን ብለዋል።
በተለይም አሁን ላይ የተዘረጋው የዲጂታል የግብር አከፋፈል ስርአት የግብር ከፋዩን ጊዜና ጉልበት የቆጠበ አሰራርንም እጅጉን ፈጣንና ቀልጣፋ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የምስራቅ ሸዋ ዞን ገቢዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ በድሪያ ረሽድ፤ በ2018 በጀት ዓመት በዞኑ 5 ነጥብ 68 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከመደበኛ፣ ከማዘጋጃ ቤታዊና ከውስጥ ገቢ የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተው የደረጃ "ሐ" ግብር መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።
በዚህም ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም ከደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ከመደበኛ እና ማዘጋጃ ቤት 140 ሚሊዮን 810 ሺህ ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 154 ሚሊዮን 890 ሺህ 135 ብር ከእቅድ በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በቀጣይም የግብር አሰባሰቡን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮችና የሰው ኃይል አደረጃጀት ተፈጥሮ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።